Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በቻግኒ ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን የሚገኙ የብራና
የእጅ ጽሑፎችን መዘርዝር መሥራት ነው፡፡ በመሆኑም አጥኚው በቤተክርስቲያኑ ውስጥ
ካሉት አጠቃላይ 71 ልዩ ልዩ መጻሕፍት መካከል ጥናቱ የሚያተኩርባቸውን ዘጠኝ የብራና
መጻሕፍትን ብቻ በመምረጥ የውጭ አካላዊ መረጃቸውን በተገቢ ኹኔታ በመግለጽ፣ በውስጥ
የያዙትን ዋናዋና ክፍል በመዘርዘር፣ የብራና መጻሕፍቱን ቅጠሎች፣ የጥራዝ ብዛቶች፣ ዐምዶች
እንዲሁም በየምዕራፉ መጀመሪያና መጨረሻ ያሉትን ይዘቶች በማየት አይነታዊ የምርምር
ዘዴን በመጠቀም የጥናቱን ውጤት ጽፏል፡፡ የጥናቱ አነሣሽ ምክንያት፣ዓላማው፣ የጥናቱ ዘዴ፣
የመረጃ መሰብሰቢያ ስልት እንዲሁም ተዛማጅ ጽሑፎች ተጠቅሰዋል፡፡ በአጥኚው የተጠኑት
ሁሉም መጻሕፍት በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ በጥናቱ መሠረትም አብዛኞቹ የብራና መጻሕፍት ከአቶ
ነጋሽ ወዳጄ የተበረከቱ ናቸው፡፡ የአቀማመጥ ኹኔታቸውም ጥሩ ስላልነበረ መጽሐፈ ብርሃን
በርጥበት ምክንያት ብራናዎቹ ጠቁረዋል እንዲሁም ተቆራርጠዋል፡፡ መዝሙረ ዳዊቱም ጠርዝ
ጠርዙ ተጎድቷል፡፡ ሌሎች ግን በጥሩ ሁኔታ ናቸው፡፡ ወንጌሉና ተአምረ ማርያም በዐበይት
በዓላት ይነበባሉ ሌሎች ግን የመነበብ እድል ተነፍገዋል፡፡ አጥኚዉ በመጨረሻዉ በማጠቃለያ
ያጠቃለለ ሲኾን ከጥናቱ በመነሣት የብራና መጻሕፍቱ ለአንባብያን ተደራሽ ቢሆኑ ሚል
የይኹንታ ሐሳብ አስቀምጧል፡፡