Abstract:
ይህ ጥናት “በገድለ አቡነ እንድርያስ ዘእፉን የይዘት ትንተና” ላይ ያተኮረ ነው። የጥናቱ
አነሣሽ ምክኒያት በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት መርሐ ግብር ስለገድላት ቅርስነት የነበረኝ
መረጃ ሲኾን፣ በዚህ ገድል ላይ ሳይናሳዊ በኾነ መንገድ የይዘት ትንተና ከዚኽ ቀደም
አለመሠራቱ እና በጽሕፈቱ ውስጥ ሰዋስዋዊ ክፍተቶች መኖራቸው ተጠቃሾች ናቸው።
ከዝርዝር ዓላማዎች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የአቡነ እንድርያስ ዘእፉን ማንነት በዝርዝር
መግለጽ፣ ማሳዎቅ፣ ገድሉ የተጻፈበትን ግእዝ ቋንቋ ሰዋስዋዊ መዋቅር መፈተሽ እና
የገድሉን ሰነ ጽሑፋዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካ ጠቀሜታ መተንተን ናቸው።
ይኽ ጥናታዊ ጽሑፍ በገድል ይዘት ትንተና ለሚያደርጉ ተመራማሪዎች እንደ መሸጋገሪያ
ድልድይ ኹኖ እንደሚያገለግል አጥኚዉ ያምናል። ጥናቱም ከዚኽ ቀደም በገድል ዙሪያ
የተሠሩ ጥናቶችን ከልሷል። ይኽን ጥናት ለማጥናት አጥኚዉ ከምርምር ዐይነቶች ውስጥ፡
ዐይነታዊ ምርምርን ዘዴን ተጠቅሟል። ለዚህ ጥናት፡ የመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጭ
የአቡነ እንድርያስ ዘእፉን ገድል ሲኾን፣ በኹለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጮች ደግሞ ከገድሉ
ጋር ተዛማጅ የኾኑ ከሌላ ገዳማት የሚገኙ ጽሑፋዊ ቅጂዎች፣ በማኅበረ ቅዱሳን
የሚታተሙ መጽሔቶች፣ ስንክሳር፣ ዐውደ ጥበብ /ኢንሳይክሎፒዲያ/፣ በባሕር ዳር
ዩኒቨርሲቲ በግእዝ ትምህርት ክፍል ለመመረቂያ የቀረቡ የጥናት መዛግብትን ተጠቅሟል።
በተጨማሪም ዓላማ ተኮር ቃለ መጠይቅ ተግባራዊ አድርጓል። በጽሕፈቱ ውስጥ ሰዋስዋዊ
ግድፈት አላቸው ላላቸው ቃላት እና ፊደላት በአራት ማእዘን ቅንፍ ውስጥ ማስተካከያ
አስቀምጧል፤ የገድሉን ሰነ ጽሑፋዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ
ተንትኗል። ገድሉ በተጻፈበት ዘመን የግእዝ ቋንቋ ድርሰት ከአሁኑ ጋር ሲነጻጸር እጅግ
በጣም ጥሩ የሚባልበት የግእዝ ቋንቋ ዕድገት ላይ ያለ ቢኾንም፣ ሰዋስዋዊ ግድፈት ግን
ጎልቶ ይታበት እንደነበር እና በተለምዶ ሞክሼ ፊደላት የሚባሉት ድምፀት፡ በባሕርየ
ፍጥረት እና በመካነ ፍጥረት ተለይተዉ በትክክለኛ ቦታቸው ያልተቀመጡበት ዘመን
መኾኑን አጥኚዉ ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
በአጠቃላይ አጥኚዉ ከዚህ ተጠኝ ገድል ያገኘው ነገር፣ ከተለመደዉ የገድል ይዘት ትንተና
በተጨማሪ፣ የፊደላትን አጠቃቀም በተመለከተ ባደረገው ጥናት፣ በገድሉ የተጠቀሱ
አንዳንድ ፊደላት ከተለመደው የግእዝ ፊደላት የወጡ መኾናቸው፣ ለዚህም ዋና ምክንያት
የጸሓፊው የዳራ ኹኔታ (Language Background) እንደኾነ ተገንዝቧል።