Abstract:
ይህ ጥናት የመድኀኒት ምጠና በመጽሐፈ ፈውስ በሚል ርእስ የተደረገ ነው፡፡ ጥናቱ በመጽሐፈ ፈውስ የባህል መድኀኒት መዝገብ ውስጥ ያለውን የመድኀኒት ምጠና መርምሮ ማሳየት ዋና ዐላማ ተደርጎ የተከናወነ ነው፡፡ ጥናቱ አይነታዊ ሲሆን ዐላማዊ የናሙና ዘዴን ተጠቅሟል፡፡ ትንተናውም በገላጭና የይዘት ትንተና ተደርጓል፡፡ ጥናቱ በውጤቱም በመጽሐፈ ፈውስ የመድኀኒት ምጠና የራሱ መልኮች እንዳሉት ለማስተዋል ተችሏል፡፡ በትንተናው እንደተስተዋለው የበሽታ መንሥኤዎች አገላለጽ ወጥነት አለመኖር፣ አልፎ አልፎም መንሥኤዎቻቸው በግልጽ አለመስፈርም፤ በተደረጉ የበሽታ ገለጻ ኺደቶች ውስጥ ምንም እንኳ ወጥነት ባይኖርም የበሽታ ገለጻ፣ መንሥኤ፣ ቅድመ መከላከል (preventative care) እንዲሁም በሽታው እንደተከሠተ ሕመምን የሚቀንሱና ዘላቂ መፍትኼ እስኪገኝ የሚደረጉ የመጀመርያ ደረጃ ሕክምና ወይም ማስታገሻ ገቢሮች ሲካተቱ ተስተውሏል፡፡ እነዚህ የማስታገሻ ገቢሮች የሰውነታችንን በሽታን የመቋቋም ኹኔታ የሚፈጥሩና የሚያሳድጉ (boost the immune system)፣ ሰውነትን ለጊዜው ከመርዙ የማከም (detoxify the body) እንዲሁም የተዛነፉ አካላዊ መስተጋብሮችን ማስተካከል (address specific imbalances) መሆናቸውንም ለመመልከት ተሞክሯል፡፡ በመጽሐፈ ፈውስ ውስጥ ሁለት ዐበይት የመድኀኒት ምጠና ሥልቶች ተመላክተዋል፡፡ እነሱም፡- ቁስ-ተኮር የመድኀኒት ምጠናዎች (Material-based dosing) እና ዝግጅት ተኮር የመድኀኒት ምጠናዎች (Preparation-based dosing) ናቸው፡፡ ከቁስ-ተኮር የመድኀኒት ምጠና አንጻር ክብደት የሚባለው እንዳልተስተዋለ፣ ይዘት በተሻለ ጥቅም ላይ እንደዋለ እንዲሁም ግልጽ ባይሆንም “ቁራጭ” የምንለው መለኪያ እንደሚስተዋል ተተንትኗል፡፡ በይዘት ረገድ ማንኪያ፣ ማንካ፣ የአረቄ መለኪያ፣ ጋን የመሳሰሉ ለመለኪያነትና ለመመጠኛነት እንዳገለገሉ ከትንተናው መመልከት ይቻላል፡፡ በቁራጭ መልኩ ደግሞ ተቀጽላ፣ ሥር፣ ቀንጠብ የሚሉ ነሲባዊ መለኪያዎች ሲያገለግሉ ተስተውሏል፡፡ ዝግጅት ተኮር የመድኀኒት ምጠናዎችን ስንመለከት በመጽሐፉ ውስጥ እንደ ማትነን (decoction)፣ አልኮል መድኀኒት (Tincture) እና የዱቄት ዝግጅት የመድኀኒት ምጠናዎች እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡ እንደ ግለሰባዊ የመድኀኒት ምጠና (Individualized dosing)፣ ቀመር-ተኮር የመድኀኒት ምጠና (Formula-based Dosing) እንዲሁም ጊዜ-ተኮር የመድኀኒት ምጠና (Frequency-based Dosing) በመጽሐፉ ውስጥ እንደሚስተዋሉ በትንተናው ተመላክቷል፡፡ ከተመሳሳይ የዕፀዋትና የተክሎች ተዋጽኦ የሚገኙ የመድኀኒት ምጠናዎች እንዲሁም ከአንድ ዕፅ ብቻ የሚገኝ የመድኀኒት ምጠና አልፎ አልፎ ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ ሲሰጡ እንደሚስተዋል፣ መካተት የሚገባው የበሽተኛው አጠቃላይ ዳራዊ ማንነት ላይ መመሥረት (ዕድሜ፣ ጾታ፣ የጤና ኹኔታ፣ ምልክቶች ወዘተ.) ወይም ሁሉአቀፍ አንጻር የምንለው ትኩረት እንደተነፈገው በትንተናው ለመመልከት ተችሏል፡፡ ግልጽ ያልሆነ የመድኀኒት ምጠና (Imprecise dosing/Lack of standardization)፣ ጥራት ላይ ማተኮር፣ ተፈጥሯዊ መፍትሔዎች (Natural Remedies) ላይ ማተኮር፣ ግለሰባዊ ልዩነቶች (Individual variations) እንዲሁም የ“Contraindications” መልክ የሚሉ መተንተኛዎች ተካተዋል፡፡ በኺደቱም ግልጽ ያልሆነ የመድኀኒት ምጠና፣ ነሲባዊ ልምድ ተኮር አሰጣጦችና ገቢሮች፣ የመድኀኒቱ የጥራት ደረጃ አለመታወቅ፣ ተፈጥሯዊ መፍትሔዎችን እንደአማራጭ መጠቀም፣ የግለሰባዊ ልዩነቶች ትኩረት ማጣት እንዲሁም መድኀኒቱን መጠቀም የሌለባቸው በተለይም ከዕድሜ፣ ከጾታ፣ ከአካላዊ ኹኔታ፣ ከነፍሰጡርነት አኳያ በበቂ ኹኔታ እንዳልተመላከተ ወይም ደካማ የ“Contraindications” ሥርዐት እንደሚስተዋል በትንተናው ተስተውሏል፡፡
ቁልፍ ቃላት፡- ባህል፣ የባህል መድኀኒት፣ የመድኀኒት ምጠና