Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በደሴ ከተማ የሚገኙ የቦታ ስሞችን ተከታታይነትና ለውጥ
መመርመር ሆኖ ተከታታይነትን ጠብቀው የሚገኙ ቦታዎችን ስያሜዎች መፈተሽ፤
የቦታ ስሞች ለውጥና የለውጥ ምክንያቶችን መለየት፤ የቦታ ስሞችን ፋይዳ
መለየት፤ የቦታ ስሞቹ ተከታታይነትና ለውጥ ላይ ማህበረሰቡ ያለውን አመለካከት
መፈተሸ የሚሉ ዝርዝር ዓላማዎችን አካትቷል፡፡ ጥናቱን ከግብ ለማድረስ የተለያዩ
መረጃዎች ከመስክ እና ከተለያዩ ሰነዶች ተሰብስበዋል፡፡ ጥቅም ላይ የዋሉት የመረጃ
መሰብሰቢያ መሳሪያዎችም፤ ቃለመጠይቅ፣ ሰነድ ፍተሻ፣ ምልከታ እና ቡድን ተኮር
ዉይይት ናቸዉ፡፡ ጠቋሚ ናሙናን በመጠቀም ለጥናቱ በመረጃ አቀባይነት የተሳተፉ
21 መረጃ አቀባዮች ተመርጠዋል፡፡ ለጥናቱ በተመረጠዉ ደሴ ከተማ የሚገኙ የቦታ
ስያሜዎችን ሁሉንም በመዉሰድ ከእነዛ ዉስጥ በእጣ ንሙና የተመረጡት የቦታ
ስሞች ለትንተና ቀርበዋል፡፡ የተሰበሰቡት መረጃዎችም በተግባራዊ ንድፈ ሀሳብ እና
በስነፍቻዊ ንድፈ ሀሳብ መሰረት ተተንትነዉ በገላጭ እና አይነታዊ የትንተና ዘዴ
ተብራርተዉ ቀርበዋል፡፡ ከመረጃ ትንተናዉም የቦታ ስያሜ መነሻ ምክኒያቶች እና
የቦታ ስያሜ የለውጥ ምክንያቶች የማህበረሰቡ ገጠመኝ፣ የሀይማኖት ተቋማት
መስፋፋት፣ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ የመሰረተ ልማት መስፋፋት፣ የንግድ እንቅስቃሴ
ወዘተ ሲሆኑ የለውጡ ሰበቦች ደግሞ የፖለቲካዊ ሥርዓት ለውጥ፣ የአካባቢው
ማህበረሰብ ስነልቡናዊ ሁኔታዎች መሆናቸውን መለየት ተችሏል፤ በተለወጡ የቦታ
ስሞች ላይም የማህበረሰቡ አመለካከት አወንታዊ ስለመሆኑ በመረጃ ትንተና
በተገኘው ውጤት ተረጋግጧል፡፡ በአንጻሩ ብዙዎቹ የቦታ ስሞች ተከታታይነትን
ጠብቀው ለመዝለቃቸው ምክንያቶቹ በማህበረሰቡ ማህበራዊ ህይወት፣ ማንነትና
ስነልቡና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር ትርጓሜና አንድምታ የሌላቸው ከመሆኑ
ጋር ሊያያዙ እንደሚችሉ መረጃዎች አመላክተዋል።