Abstract:
አጠቃሎ
ይህ ጥናት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በዝቋላ ወረዳ በሚከበረው የሽውዬ እና ምሻምሾ ባህላዊ ጨዋታ ክዋኔ እና ፋይዳ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር ። ጨዋታው በአማርኛ ዥዋዥዌ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በኽምጣጛ ቋንቋ ወይም በመገኛ ቋንቋው እሽውዬ ተብሎ ይጠራል ፡፡ስለሆነም እኔም በመገኛው ቋንቋ ያለውን እሽውዬ የሚለውን ስያሜ ጥናቴ ላይ ተጠቅሜበት አለሁ፡፡
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማው ደግሞ ክዋኔና ፋይዳውን መመርመር ነው ፡፡ የጥናቱን ዓላማ ለማሳት ትኩረት የተሰጠው ጨዋታው ያለውን የክዋኔ ሂደትና ጨዋታው የሚያበረክተውን ፋይዳዎች የሚያሳዩ የምርምር ጥያቄዎችን በማዘጋጀት በምልከታ ፣በቃለ መጠይቅና በተተኳሪ የቡድን ውይይት የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም መረጃው ከመስክ ተሰብስቧል ፡፡
በዚህም መሠረት በዝቋላ ወረዳ የሽውዬ እና ምሻምሾ ባህላዊ ጨዋታ ክብረ በዓል ወቅት ከክበረ በዓሉ ጅማሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ ያለውን ክዋኔ ሲከውኑ የሚገጠሙ የቃል ግጥሞችን ፋይዳዎችን በየወገናቸው በመመደብ ተተንትነዋል፡፡ በዚህ ጥናት ማህበረሰቡ በክዋኔዎች አማካይነት በቀጥታና በጎንዮሽ ሃሳቡን በመግለፅ ሲያስተምሩበት፣ ሲመክሩበት፣ ሲያዝናኑበት፣ ሲያስተላልፉበትና ባህላዊ ማንነትቱን ሲያስጠብቁበት መቆየቱን ማረጋገጥ ተችሏል።
ትንታኔ የተደረገው በዋናነት መረጃዎቹ ከተሰበሰቡበት አውድ አኳያ የይዘት ትንተና የተጠቀመ ሲሆን ክዋኔው በማህበረሰቡ ውስጥ ካለቸው ፋይዳ አንጻር ደግሞ የክውና ንድፍ ሃሳብን፣ የቁሶችን ውክልና እና ተግባራዊ ንድፍን ሃሳብን መሠረት ያደረገ ነው። በክዋኔው አማካይነት የሚተላለፉ ቁምነገሮች እና የሚከወኑ ክዋኔዎች የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ መስተጋብር የማስተማር ሚና እንዳላቸው የጥናቱ ውጤት ያሳያል። በመሆኑም ለወጣቱ ትውልድ ማስተማርያነት ማዋል እንደሚቻል በጥናቱ መደምደሚያ እና ይሁንታ ውስጥ በዝርዝር ተገልጸዋል።