Abstract:
ይህ ጥናት በዕፀ ደብዳቤ ኆኅተ ብርሃን የባህል መድኃኒት አተገባበር ትንተና በሚል ርእስ የቀረበ ነው። የምርምሩ ዋና ዓላማ በዕፀ ደብዳቤ ኆኅተ ብርሃን የሚገኙትን የባህል መድኃኒቶችን አተገባበር መመርመር ነው፡፡ መናፍስት ርኩሳን ማለት ምን ማለት ነው? በዕፀ ደብዳቤ ኆኅተ ብርሃን የባህል መድኃኒት አተገባበርና የሕመም ዓይነቶች፤ የዕፀዋቱ አገልግሎት ምን ይመስላል? ባህላዊ መድኃኒት ለዘመናዊ መድኃኒት ምን ዐይነት አስተዋጽዖ አበርክቷል፣ አኹንስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሚሉትን ይዘቶች ከመጽሐፉ አንጻር ለመፈተሸ የታለመ ነው፡፡ የጥናቱ አነሣሽ ምክንት ባህላዊ መድኃኒት በዘፈቀደ የሚሰጥ ነው የሚል እና የባህል መድኃኒት መጽሐፍት፤ አንዲሁም የባህል መድኃኒት ባለሙያዎች ሕመሙ አንድ ሲኾን የተለያዬ መድኃኒት መኖሩ የሚለውን ሐሳብ የሚገልጽ ነው፡፡ የጥናቱ መረጃም በዋናነት በሰነድ ፍተሻ ተሰብስቧል፡፡ ምርምሩም ከዓይነታዊ የምርመር ዘውግ የሚመደብ ሲኾን መረጃውም በገላጭ ዘዴ ተተንትኖ ቀርቧል፡፡ ለዘመናዊ ሕክምና መሠረቱ ባህላዊ ሕክምና ወይም ባህላዊ መድኃኒት መኾኑ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ አኹን ላይ ዘመናዊ መድኃኒት በመስፋፋቱ በህላዊ መድኃኒት እየተረሳ መምጣቱን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ በዕፀ ደብዳቤ ኆኅተ ብርሃን የተገለጡ የሕመም ዓይነቶች፣ መድኃኒቶቹ እና ገቢራቸው በቅደም ተከተል ቀርበዋል፡፡ ዕፀ ደብዳቤ ኆኅተ ብርሃን በመጀመሪያው ክፍል ስለባህል መድኃኒት የሚያትት ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጸሎተ ዕጣን፣ የሰዋስው ትርጕም፣ ጠቢበ ጠቢባን፣ መፍትሔ ሥራይ፣ ጸሎተ ቡዳ እና ጸሎተ ነሐቢ (ሠራተኛ) በቅደም ተከተል ቀርበዋል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ የዕፀዋቶቹ ብዛት እና አገልግሎት እንዲሁም መገኛ ሥፍራዎች እና የሚሰጡት ጥቅሞችም የተገለጹ ሲኾን የሕመም ዓይነቶች፣ መድኃኒቶቹና መገኛ ቦታቸውን፣ የሚሰጡት የፈውስ ዓይነትና ገቢራቸውን ጥናቱ አሳይቷል፡፡ መድኃኒቶቹም በመታጠን፣ በሚቀባ፣ በሚዋጥ፣ በመታጠብ፣ በሚጠጣ እና በሚበላ መልኩ እየተመጠኑ የሚሰጡ መኾኑን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም ወተት፣ ጠላና ማር፣ ደግሞ ለመድኃኒቱ ማዋሐጃነት ይውላሉ፤ ነገር ግን በሽታው ሲበረታ ማርከሻ ወይም ማስታገሻ እርጎ እና ጠላ መጠጣት አስፈላጊ ነው፡፡ እንዲሁም መድኃኒቱ እንዲሠራ ከአልኮል፣ ከሰው ጥላ (ግብረ ሥጋ ግንኙነት ከፈጸመ እና ፀሐይ ሲመተው ቆይቶ ከሚመጣ ሰው) እና ከግብረ ሥጋ ግንኙነት መጠበቅ ግዴታ እንደኾነ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ በመጨረሻም ጥንታዊ የባህል መድኃኒት መዛግብትን መልሶ ለማግኘት እና ለመመራመር እንደመነሻ ኾኖ እንደሚያገለግል እና ለተጨማሪ ጥናት መነቃቃትን ሊፈጥር እንደሚችል ተመላክቷል፡፡