Abstract:
ይህ ጥናት የግራር ጃርሶ ወረዳ ማህበረሰብ ፈጫሳን እንደ ህይወት ዑደት ማስጠበቂያ ስርዓት
የተጠቀመበት ሁኔታ መመርመር የሚል አብይ አላማ ያለው ሲሆን ለዚህ አላማ ከግብ
መድረስ ደግሞ በስርዓተ ከበራው አጀማመር (ሚቱ) እና በስርዓተ ከበራው መካከል ያለውን
ግንኙነት መመርመር፣ በክዋኔው ውስጥ ያሉ ልማዶችና ልማዶችን ለመከወን አገልግሎት
ላይ የሚውሉ ቁሶች በማህበረሰቡ ህይወት ውስጥ ያላቸውን ፋይዳ ማስረዳት እንዲሁም
በስርዓተ ከበራው ክዋኔ ወቅት የሚከወኑ ሃገረሰባዊ ሙዚቃዎች ቃል ግጥሞች ይዘት
በመመርመር የማህበረሰቡን ሕይወት ከማስጠበቅ አንጻር ያላቸውን ፋይዳ መፈተሸ የሚሉ
ዝርዝር አላማዎች የተመረመሩበት ነው፡፡ ጥናቱ አይነታዊ የምርምር ዘዴን የተከተለ ሲሆን
በጥናቱ ለመረጃ አቀባይነት የተሳተፉ ሰዎችም በአላማ ተኮር እና ጠቋሚ የናሙና አመራረጥ
ዘዴዎች ተመርጠዋል፡፡ የመስክ መረጃዎች በምልከታ፣ ቃለመጠይቅ እና ተተኳሪ ቡድን
ውይይት በመታገዝ የተሰበሰቡ ሲሆን በሚት ሪችዋል ቲዎሪ የመረጃ መቀንበቢያነት በገለጻ
እና የይዘት ትንተና ዘዴዎች ተተንትነዋል፡፡ ከትንታኔውም በተገኘው ሃሳብ መሰረት ፈጫሳ
ስርዓተ ከበራ ተጠኚው ማህበረሰብ ድሮ ብሎ በሚጠራው ጊዜ የኖረች አንዲት የማህበረሰቡ
አባል ልጅ ያለመውለድ ችግር ገጥሟት ይህን ችግር ላስወገደችላት አማልክት አሷ እና
እንደሷ አይነት ችግር የገጠማቸው የማህበረሰቡ አባላት ችግራቸው ይፈታላቸው ዘንድ
እንዲከውኑት በታዘዙት መሰረት የግራር ጃርሶ ወረዳ ማህበረሰብም ዛሬ ድረስ በህይወት
ሲኖር ባለታሪኳ የደረሳትን በረከት ያገኝ ዘንድ፣ ለመኖሩ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮች
እንዳይከሰቱበት አስቀድሞ ለመከላከል እና የተከሰቱበትን ችግሮችንም ለማስወገድ ሲል
ለአማልክቷ ልመና እና ምስጋና የሚያቀርብበት ስርዓታዊ ከበራ ነው፡፡ የዚህ ስርዓተ ከበራ
ክዋኔ ከአጀማመሩ ወይም ከሚቱ ጋር ዝምድና ያለው እና መንፈሷን ከመለመን ውጭ ደግሞ
በተወሰኑ ስርዓቶች የተለየ ነው፡፡ በፈጫሳ ስርዓተ ከበራ ላይ የሚከወኑ ስርዓታዊ ልማዶች
ዘር ለመተካት፣ ለከብቶችን እርባታ፣ ለሰብል ዕድገት፣ ማህበራዊ ትስስርን ለመፍጠር፣ ሰላም፣
ጤናንና በረከትን ለማግኘት እና ወደተሻለ ኑሮ ለመሸጋገር በማገልገል የማህበረሰቡን
የህይወት ዑደት ማስጠበቂያ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በስርዓተ ከበራው ላይ የሚከወኑ ሃገረሰባዊ
ሙዚቃዎች ቃል ግጥሞች እና በተለያዩ ልማዶች ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ቁሶች
ማህበረሰቡ ስርዓተ ከበራውን ለሚከውንላት አማልክት ለመለመኛናነት ለማመስገኛንት
በመጠቀም ሕይወቱን ለማስጠበቅ የሚገለገልባቸው ናቸው፡፡