Abstract:
ይህ ጥናት በጦርነት ወቅት የተገጠሙ የሽለላና ፉከራ ግጥሞችና ተግባራቸው በሰሜን
ጎንደር ዞን፣ በደባርቅ አካባቢ ላይ ምልከታ አድርጓል፡፡ የጥናቱ ዐቢይ ዓላማ በሰሜን
ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ደባርቅና አካባቢዋ ባሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የተገጠሙ የሽለላና
ፉከራ ግጥሞችና ተግባራቸው፣ የቃል ግጥሞች ይዘት ትንተና፣ ቴክኒኮችና ዐውዶች
እንዲሁም ለውጦችን መመርመር ነው፡፡ በጦርነትና በቅስቀሳ ወቅት የተገጠሙ የቀረርቶና
የፉከራ ግጥሞችን ክዋኔ መግለጽ፣ ይዘታቸውን ማሳየት/መተንተን፣ ማህበረሰቡ ሽለላና
ፉከራ በፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅሞች ማሳየት ላይ ስለሚኖራቸው አበርክቶ የሚሉና
ሌሎች ንዑሳን ዓላማዎችም አሉት፡፡ ጥናቱን ለማካሄድ መረጃዎች በምልከታ፣ በቃለ መጠይቅና በተተኳሪ ቡድን ውይይት ተሰብስበዋል፡፡ የተሰበሰቡ መረጃዎች በክዋኔ ተኮር
ንድፈ ሃሳብ እና በስነ-ልቦና ንድፈ ሀሳቦች እይታ በማድረግ ተፈትሸዋል፡፡ መረጃዎቹን
የተነተንኩት ክዋኔ መር ንድፈ ሃሳብና ስነልቡናዊ ንድፈ ሃሳብ በመመራት ገላጭ
(Descriptive) እና የይዘት ትንተና (Content Analysis) ዘዴዎችን ተጠቅሜያለሁ፡፡ ገላጭ
የመተንተኛ ዘዴን የመረጥኩት በሽለላና ፉከራ ስርዓት ላይ የሚኖረውን ልዩ ልዩ ክዋኔ
(እንቅስቃሴያቸውን፣ ስሜቶቻቸውን፣ ቁስ አጠቃቀማቸውን. . .) ስዕላዊ በሆነ መልኩ
መግለፅ የሚያስችለኝ ስልት በመሆኑ ነው፡፡ በጥናቱ ውጤትም ሽለላና ፉከራ በጦርነት
ወቅቶች ሊከወን የሚችለው በሶስት ሂደቶች ውስጥ እንደሚሆን አመላክቷል፡፡ አንደኛው
ለቅድመ ጦርነት መቀስቀሻ ስልት የሚከወን ሲሆን ይሄም የማህበረሰብንና የተዋጊን
ስነልቡና በእጅጉ በመቀስቀስና በማቀጣጠል ረገድ ከሁሉም ስልቶች በላቀ አይነተኛ ሚና
መጫወት መቻሉን ያሳያል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በራሱ ጦርነቱ እየተደረገ ባለበት ወቅት
የሚቀርቡ የጀግና ግጥሞች ሲሆኑ በውጊያው የተመቱም ሆነ ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት
በማነቃቃትና ብርታት በመስጠት ሽለላና ፉከራ ምን ያህል ጠቃሚ አበርክቶ እንዳላቸው
አሳይቷል፡፡ የመጨረሻው ደግሞ ከድህረ ጦርነት ማግስት ስለሚገጠሙ የጦር ሜዳ ወይም
የጀግና ግጥሞች ሲሆን የማህረሰብን ስነ ልቡና በመገንባት፣ የወደሙ ሃብታና ንብረቶችን
መልሶ ስለመጠገን እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት ሚና ያላቸው አካላት ወይም ግለሰቦች
እንዴት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚታወሱ ጭምር በግጥሞች
አማካኝነት የሚገለጹበትን ሁኔታ የሚያሳይ የጥናት ውጤት ነው፡፡ ሌሎች አሁናዊ የጦር
ሜዳ ግጥሞች ምን ይዘትና ስልት ላይ ትኩረት እንዳደረጉ በማሳየት ትውልዱ አሁናዊ
ግንዛቤው ምን እንደሚመስል አዲስ እውቀት ይሰጣል፡