Abstract:
ይህ ጥናት ቃል ግጥም ለባህል እሴት ግንባታ ያለው ፋይዳ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ
በሚል ርዕስ የተደረገ ጥናት ነው፡፡ ለጥናቱ አነሳሽ የሆነኝ ምክንያት ጥናቱ ትኩርት ያደረገባቸው
አካባቢዎች፡-የኦሮሞ፣የአገው እና የአማራ ብሔርሰብ ክፍሎች ለረጅም ዘመናት በጋራ ተከባብረው፣
ተዋደው በአብሮነት ይኖራሉ፡፡ ይህን ማህበርሰብ በጋራ አደጋግፈው እና አፋቅርው በአብሮነት ያቆዩት
ማህበረሰባዊ እሴቶች ምንድን ናቸው ፡፡ እነዚህ እሴቶችን ለማጠናከር በማህበርሰቡ የሚፈጠሩ ቃል
ግጥሞች ተዘርዝረው አልተጠኑም ስለሆነም እሴታቸውን የሚያጠናክሩባቸው ቃል -ግጥሞች እየተረሱ፣
እየተለወጡ በሂደትም እየጠፋ የመሄድ አጋጣሚዎች ሰፊ ነው፡፡ በነዚህም ምክንያቶች ጥናቱ ወቅታዊ
እና አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ለጥናቱም የተመረጡ አካባቢዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ
ወረዳ የቁጭ፣ ዋድራና ቦቆጣቦ ቀበሌዎች ናቸው፡፡የጥናቱ አላማ በማህበርሰቡ እሴት ግንባታ ላይ ጉልህ
ፋይዳ ያላቸው ቃል-ግጥሞች መሰብሰብ፣መተንተን ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ቃል-ግጥሞች ለማህበረሰብ እሴት
ግንባታ ያላቸውን ፋይዳ መሰብሰብና መተንተን፡፡ በቃል-ግጥሞች አማካኝነት የማህበርሰቡ እሴት
መግለፅ፡፡ እነዚህን አላማዎች ለማሳካት መስክ ላይ የተሰበሰቡ ቃል ግጥሞች 106 ናቸው፡፡ ከነዚህ ቃል
ግጥሞች ውስጥ በማህበረሰቡ እሴት ግንባታ ጉልህ ፋይዳ ያላቸው 32/ ሰላሳ ሁለት/ ቃል-ግጥሞች
በስምንት/8/ የማህበርሰብ እሴቶች በሚያንፀባርቅ መልኩ በተግባራዊያን፣በስነ-ልቦና ተግባራዊያን እና
በታሪክ ጠቀሜታ ንድፍ ሀሳብ ተተንትነዋል፡፡ቃል-ግጥሞችን ለመሰብሰብ የተጠቀምሁባቸው የመረጃ
መሰብሰቢያ ዘዴዎች፣ቃለ መጠየቅ፣ቡድን ተኮር ውይይት፣ሰነዶችን መፈተሽ ሲሆን በፎቶ ግራፍ፣
በቪዲዬና በማስታዎሻ የታገዙ ናቸው፡፡ቃል-ግጥሞች ካላቸው የማህበረሰብ እሴት ግንባታ አኳያ አብሮ
መብላት፣መጠጣት፣በፍቅርና በጋብቻ ዝምድና ፈጠራ፣የታመመን ማየትና የመርዳት፣የተጣላን
ማስታርቅ፣የተጎዳን ማፅናናት፣ወንጀለኛን የመገሰፅና የማስተማር፣የሞተን አልቅሶ የመቅበርና የማፅናናት
ፋይዳዎች የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ምደባ በተደረገው ትንተና ጥናቱ ከደረሰባቸው ግኝቶች
መካከል ማህበረሰቡን ለረጅም ዘመናት በጋብቻ የተዛመደው ሰው በመሆኑ ብቻ እና በማህበረሰቡ
ያላቸው ተቀባይነት፣ ለስራ ያለው ታታሪነት እንጂ ብሔር ተኮር ጋብቻ የለም፡፡ የታመመን የማህበረሰብ
ክፍል ከማሳከም ባሻገር፣ወቅቱ የሚፈልገውን ተግባር በጋራ መስራት፣ መረዳዳት የተጎዳን ማፅናናት
የተጣላን ማስታርቅ፣ የሁሉም የማህበርሰብ ክፍል ማህበር ህግጋት ነው፡፡እንግዳ መቀበል፡ የማህበረሰቡ
ብቻ ሳይሆን ዋርካዎችም ታሪካዊ ተጠቃሽ መሆኑን ማሳየት ተችሏል፡፡ቃል ግጥሞች ለባህል እሴት
ግንባታ ያላቸውን፣ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን የጥናቱ ውጤት
ያሳያል፡፡ ስለሆነም የሚመለከታቸው የማህበረሰብ ክፍሎች፣የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የስነ-ጽሁፍ
ባለሙያዎች፣የህዝብ አስተዳዳሪዎች፣ የትምህርት ባለሙያዎች ወዘተ… ይህንን ጥናት እንደመነሻ
በመጠቀም ህብርተሰቡን ለማስተዳደርና ለልማት ቢገለገሉበት ተጨማሪ ጥናቶች ቢካሄዱበት መልካም ነው፡፡