Abstract:
ይህ ጥናት በዋናነት በይጎማ ሁለቱ ማህበረሰብ ዉስጥ የለቅሶ አዉድን በመመልከት ጀግንነት እንዴት እንደተሳለ በፉከራ ቃል- ግጥሞች ይዘትና ክዋኔ አማካይነት እሳቤዉን የመረመረ ነዉ ፡፡ በዚኽም የጀግና ምንነት፣ መገለጫዎች ፣ አፈጣጠር፣ አቀራረጽ፣ የእሴቱ መጠበቂያ ስልትና ፋይዳዎችን ለመዳሰስ ተችሏል ፡፡ እነኚህ የጥናቱ አለማዎች ግባቸዉን ይመቱ ዘንድ መረጃዎች ከቀዳማይና ከካልኣይ የመረጃ ምንጮች ተሰብስበዋል፡፡ በይጎማ ሁለቱ ቀበሌ የሶስት ጀግና የለቅሶ ስነ- ስርአት ላይ በመታደም በምልክታ፣ በቃለመጠየቅና በተተኳሪ ቡድን ዉይይት 22 የመረጃ አቀባዮች በዓላማ ተኮር የመረጃ ዘዴ ተመርጠዉ መረጃዎች ተሰብስበዋል ፡፡ መረጃዎቹም በፎቶ፣ በቪዲዮ ካሜራ፣ በመቅረፀ ድምፅ፣ እና በማስታወሻ ደብተር ተይዘዋል፡፡ ከከልኣይ የመረጃ ምንጮች ደግሞ ስምንት ተዛማጅነት ያላቸዉ ቀደምት ጥናቶች እንዲሁም የተለያዩ ፅንስሃሳቦች ተቃኝተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተሰበሰቡ ጥናቶች በአግባቡ ተደራጅተዉ በክዋኔያዊ እና ተግባራዊ ንድፍ ሀሳቦች ተተንትነዋል፡፡ በትንታኔዉም ጀግና ማለት ከብዙሃኑ የማሀበረሰብ አባላት በተለየ መልኩ ሰርተዉ በማሳየት ከፊት ሆነዉ የሚመሩ፣ በተፈጠሩበት ማህበረሰብ ዉስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸዉ፣ የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ገፅታ የያዙ የማህበረሰቡ ወኪሎች ናቸዉ ከሚል ተግባራዊ ብያኔ ላይ ተደርሷል፡፡ በኢኮኖሚ ከፉተኛ ደረጃ ላይ መድረስ፣ የተጣሉ ሰዎችን ማስታረቅ፣ ለጋስ መሆን፣ የሀገርን ዳር ድንበር ማስከበር፣ አካባቢን በስረዓት ማስተዳደር፣ ደምን መመለስ እና በባልትና ስራ ልቆ መገኘት ደግሞ የጀግንነት መገለጫዎች ሆነዉ ተገኝተዋል፡፡ የእነኒህ ጀግኖች መፈጠር ዋነኛ ምክንያት ሆኖ የተገኘዉ በአለፉት ጊዚያቶች በተለያየ መልኩ በማህበረሰቡ ላይ የተደቀኑ ችግሮች/ፈተናዎች / መኖራቸዉ እንደሆነ፣ ከስነ-ቃል አይነቶች መካከልም ቃል- ግጥሞች የይጎማ ሁለቱ ማህበረሰብ ጀግናዎቹን የሚቀርጽባቸዉ እንደሆኑና የቤተሰብና የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ ልጆች ጀግና ሆነዉ እንዲታነፁ የማይተካ ድርሻ አንዳላቸዉ እንዲሁም ጀግንነት ኢ- መደበኛ በሆነ መልኩ እንደሚለመድ ለማወቅ ተችሏል ፡፡ ማህበረሰቡ ይሂንን የጀግንነት እሴቱን የሚያስጠብቀዉ የጀግናዎቹን ከፍ አድርጎ በመመልከትና ተገቢዉን እዉቅና በመስጠት እንደሆነ፣ የጀግኖች መኖርም የኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅሞች እንዳሉት የተረጋገጠ ሲሆን በአጠቃላይ የይጎማ ሁለቱ ማህበረሰብ የጀግና እሳቢዎች የማህበረሰቡን እሴቶች መጠበቂያ፣ የማህበረስቡ የአኗኗር ዘይቤ መገለጫ እና ማህበረስቡ በልዩ ልዩ መልኩ ያለዉን የህይወት ፉልስፉናዎቹ ማሳያዎች እንደሆኑ የጥናቱ ዉጤቶች ሁነዉ ተገኝተዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት በየቀበሌዉ ዉስጥ ማናቸዉም የልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ከመሆናቸዉ በፊት የማህበረስቡን የጀግንነት እሳቤ መነሻ ያደረጉ ቢሁኑ፣ በጥናቱ የተዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች የሚመለከቷቸዉ ባለድርሻ አካላት ይኽንን የጀግንነት እሳቤ በአንክሮ በመመርመር ማህበረሰቡን በተሻለ መልኩ ለማገልገል በግብአትነት ቢጠቀሙበት የሚሉና መሰል ይሁንታወች ተሰጥተዋል፡፡