Abstract:
አጠቃሎ
ይህ ጥናት በእንጅባራ ከተማ ማህበረሰብ አለባበስና አጊያጊያጥ ውስጥ የተከሰተውን
ባይተዋርነት መመርመር የሚል አብይ ዓላማ አለው፡፡ ለዚህ ዓላማ መሳካት ደግሞ የተጠኝው
ማህበረሰብ ነባር መገለጫ የሆነውን ሀገረሰባዊ አለባበስና አጊያጊያጥ እንዲሁም የማስቀጠያ
ስልቶችን ማሳየት፤ በማህበረሰቡ የአለባበስና አጊያጊያጥ ስርዓት ውስጥ የተከሰተውን
ባይተዋርነት መመርመር፤ ለባይተዋርነቱ መከሰት ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች እና ክስተቱ
ያስከተላቸውን ተፅዕኖዎች ማብራራት የሚሉ ዝርዝር አላማዎች ተብራርተውበታል፡፡ ጥናቱ
አይነታዊ የምርምር ዘዴን የተከተለ ነው፡፡ በጥናቱ ውስጥ ለመረጃ አቀባይነት የተሳተፉ
ሰዎችም በዓላማ ተኮር እና ጠቋሚ የናሙና አመራረጥ ዘዴዎች ተመርጠዋል፡፡ የመስክ
መረጃዎች በምልከታ፣ ቃለ መጠይቅ እና ተተኳሪ ቡድን ውይይት በመታገዝ ተሰብስበዋል፡፡
የተሰበሰቡት መረጃዎችም በተሃድሶ ሥነልቡናዊና የባይተዋርነት ንድፈ ሃሳቦች መቀንበቢያነት
በገለጻ እና ማብራሪያ ዘዴዎች ተተንትነዋል፡፡ በትንታኔው ግኝት መሰረትም የእንጅባራ
ማህበረሰብ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በማህበራዊ ደረጃ፣ በመለበሻ አውድና ምክንያት ላይ የተመሰረቱ
የአለባበስና አጊያጊያጥ ስርዓቶች ያሉት መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡ እነዚህንም ማህበረሰቡ
ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስቀጥልባቸው ስልቶች ውርስ፣ ኃይማኖታዊና ማህበራዊ ህግና
ደንቦች፣ ማንነትን የመግለጽ ፍላጎት፣ የእርስ በርስ ውድድርና በልዩ ልዩ ማህበረሰባዊ ኩነቶች
በሚካሄድ ሽግግር መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማህበረሰቡ
የአለባበስና አጊያጊያጥ ስርዓት ውስጥ ያልተለመዱ ባይተዋር ክስተቶች እየተስፋፉ መጥተዋል፡፡
ለእነዚህ ክስተቶች መፈጠር ምክንያቶችም የከተሜነት መስፋፋት፣ የፈጠራ ስራዎች እድገት፣
የመገናኛ ዘዴዎች መስፋፋት፣ የተስተላልፎ ችግርና የአቻ ግፊት መሆናቸው ታቀወቋል፡
በመጨረሻም እነዚህ የባይተዋርነት ክስተቶች በእንጅባራ ማህበረሰብና ባይተዋር የሆነ
የአለባበስና አጊያጊያጥ ስልትን በሚከተሉ የማህበረሰቡ ክፍሎች ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣
ስነልቦናዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖዎች እንዲሁም የጤና ችግሮች እያስከተሉ መሆናቸውን
መረዳት ተችሏል፡፡