Abstract:
የዚህ ጥናት ዓብይ ዓላማ በእነብሴ ሳርምድር ወረዳ በሳርምድር ቀጠና ማህበረሰብ በባህላዊ ጋብቻ ስርዓት ውስጥ የሚከወኑ ሀገረሰባዊ እምነቶች አንድምታና ፋይዳ ተንትኖ ማሳየት ነው፡፡ ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የባህላዊ ጋብቻ ስርዓት ክዋኔ ምን ይመስላል? በባህላዊ የጋብቻ ስርዓት ውስጥ የሚከወኑ ሃገረ ሰባዊ እምነቶች አንድምታ ምን ይመስላል? በባህላዊ የጋብቻ ስርዓት የሚከወኑ ሃገረ ሰባዊ እምነቶች ፋይዳ ምንድን ነው? የሚሉ መሪ ጥያቄዎች ተነስተው በጥናቱ ምላሽ አግኝተዋል፡፡ እነዚህን መሪ ጥያቄዎች ለመመለስ ጥቅም ላይ የዋሉ መረጃዎች ከቀዳማይና ከካልኣይየመረጃ ምንጮች መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ ከቀዳማይ የመረጃ ምንጮች በምልከታ፣በቃለ መጠይቅና በቡድንተኮርወይይት መረጃዎች የተሰበሰቡ ሲሆን በካልአይ የመረጃ ምንጮች ደግሞ ከጥናቱ ተዛማጅነት ያላቸው ሰነዶች፣ ጽንሰ ሃሳቦች እንዲሁም አራት የቀደምት ጥናቶች ተቃኝተውቀርበዋል፡፡ከቀዳማይና ከካልኣይ የመረጃ ምንጮች የተሰበሰቡ መረጃዎች በፈርጅበፈርጅተደራጅተው በተግባራዊ ንድፈ ሀሳብ ተተንትነዋል፡፡ የመረጃ ትንተናው ውጤት እንደሚያሳየውበባህላዊ ጋብቻ ስርዓት ከቅድመ ጋብቻ እስከ ድህረ ጋብቻ ድረስ የሚከወኑየተለያዩ ክዋኔዎች ያሉ ሲሆን ከጋብቻ በፊት የመተጫጨት፣ የሚስት ጥየቃ፣ የቀን ቆረጣና ትምንምን፣ የብቅል ሰበራ፣ የዳስና የጫጉላ ስራዎች ሲከወኑ በባህላዊ ጋብቻ የሰርግ ዕለት በተጋቢ ቤተሰቦች ቤት ከጥዋት እስከ ማታ በርካታ ተግባራት ይከወናሉ፡፡በሰርጉ ማግስትና ሳልስት በወንድና በሴት ሙሽራ ቤተሰቦች ቤት የዳስ ማፍረስ ስርዓት ተመሳሳይ ክዋኔ ሲኖረው በወንድ ሙሽራ ቤት ከጫጉላ ቆይታ በኋላ አዳራሽ መግባትና ስም ማውጣት በሰርግ ፍጻሜ ዕለት የሚከወኑ ዓበይት ክዋኔዎች ናቸው፡፡በባህላዊ ጋብቻ ሥርዓት የሚከወኑ ሀገረሰባዊ እምነቶችን በመከወን ጋብቻ መፈፀሙ ለተጠኚው ማህበረሰብ ወደፊት በህይወቱ ውስጥ ይህን አገኝ ይሆናል የሚል አንድምታ ያላቸውና በአንፃሩ ተጠኝው ማህበረሰብ እነዚህን እምነቶች ሳይከውን ጋብቻ የሚፈፅም ከሆነ በህይወት ሳለ የሚያጣቸው የተለያዩ አንድምታዎች ያሏቸው ሀገረሰባዊ እምነቶች እንዳሉ የጥናቱ ውጤት ያሳያል፡፡በባህላዊ ጋብቻ ስርዓት ሀገረሰባዊ እምነቶች መከወናቸው ለባህሉ ባለቤት ከተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችና ክስተቶች ለመዳን ስነልቦናዊ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ፣ወደ ፊት በህይወቱ ጥሩና የተሻለ ነገር ለማግኘት ተስፋ እንዲኖረው፣ በማህበረሰቡ ዘንድ ማህበራዊ ተቀባይነትእንዲኖረውናቁሳዊና መንፈሳዊ የሆኑ ሀብቶቹን በመጠበቅ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለለፍ የሚያስችሉ ፋይዳዎች እንዳሉት የጥናቱ ውጤት ያሳያል፡፡ ከጥናቱ ውጤትበመነሳት ከቅድመ ጋብቻ አስከ ድህረ ጋብቻ ድረስ ባለው የሰርጉ ሂደት ከጋብቻው የተለያዩ ክዋኔዎች ጋር አብረው የሚከወኑ የራሳቸው የሆኑ አንድምታዎች ያሏቸው ሀገረሰባዊ እምነቶች እንዳሉና የባህሉ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብምበጋብቻ ስርዓት እነዚህን እምነቶች በመከወኑ የሚያገኛቸው በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ከዚህ በመነሳት ተጠኚው ማህበረሰብ እምነቶችን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲችል ለእነዚህ እምነቶች ትኩረት ተሰጥቷቸው የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ የወረዳው ባህልና ቱሪዝም የበኩሉን ድርሻ መወጣት ቢችል የሚሉና ይህ ጥናት ባልዳሰሳቸው ሌሎች ሀገረሰባዊ እምነቶች ላይ ሌሎች አጥኚዎች የተጠናከረ ጥናት ቢያካሂዱ የሚሉ የይሁንታ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡