Abstract:
አጠቃሎ
ይህ ጥናት ነውር እንደማህበራዊ ደንብ ማስጠበቂያ ስልትነት በዶርዜ ማህበረሰብ በሚል ርዕሰ
ጉዳይ የተጠና ነው፡፡ የጥናቱ አላማ በማህበረሰቡ አስተሳሰብና አመለካከት ውስጥ ነውር ያለውን
ቦታ በመመርመር የማህበረሰቡን አስተሳሰብ አመለካከትና እውቀት መግለጽ ነው፡፡ የጥናቱን
አላማ ከግብ ለማድረስ በዋነኝነት ቃለ መጠይቅ፣ ቡድን ተኮር ውይይት፣ ምልከታ እና
መዛግብት ፍተሻ በማካሄድ መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ የጥናቱ አይነት አይነታዊ ገላጭ ምርምር
ነው፡፡ በጥናቱ ተሳታፉ የነበሩ ሰዎች በአላማ ተኮር እና ጠቋሚ ናሙና ስልት የተመረጡ
ናቸው፡፡ በመረጃው መሰረትም ክብርን ከማስጠበቅ አንጻር፣ በሌላ ወገን ላይ በሚደርሱ ነገሮች፣
ዝምድናን ከማስጠበቅ፣ የትዳርን ሕልውና ከማስጠበቅ ጋር ፣ለሴቶች የሚከለከሉ እና ከእምነት
ጋር ተያያዥ ነገሮችን ጉዳይ ያደረጉ 52 ነውሮች የጥናቱ አካል ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ ላይ
የተደረገው ምደባና ትንተና ይዘታቸውን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ከክብር ጋር ተያያዥ ነውሮች
የመከባበር እሴትን ለማስጠበቅና ለማስቀጠል ማህበራዊ ደረጃን ቅደመ ተከተላዊ ስርአቱን
ለማስጠበቅ ነው፡፡ በሌላ ወገን ላይ ከሚደርሱ ነገሮች ጋር የሚገለጹ ነውሮች ደግሞ እርስ በርስ
የመረዳዳትና የመተሳሰብ እሴትን ለማስጠበቅ በስነ ምግባር የታነጹ ለወገን ደራሽ ትውልድ
ለማፍራት ነው፡፡ ከዝምድና ጋር ተያያዥ ነውሮች በቤተ ዘመድ መሀል ያለውን የደም ትስስር
እንዳይፈርስ፣ የሚወደደውን ለማቅረብ የሚጠላውን ለማራቅ ሲሉ ነውሮችን ይፈጥራሉ፡፡
ትዳርን ከመሰረቱ በታማኝነት በመቻቻል የተሞላ እንዲሆን፣ ለሴቶች ደግሞ ጾታን መሰረት
ያደረጉ ክልከላዎችን ከሀይማኖታዊ ስርአት ጋር በማያያዝ እና ከንጽህና ጋር በተያያዘ ርኩሰትን
ስለሚያመጡ፣ ከእምነት ጋር የሚያያዙ ነውሮች ደግሞ ማህበረሰቡ ከሰው ልጆች ውጭ ያሉ
መብረቅ፣ እባብና ነብርን እንደመልዕክተኛ ይቆጥሯቸው ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል አንደኛቸው
ቢከሰቱ በቤተሰቡ ላይ መቅሰፍትን ሞትን ስለሚያመጡ የሚሉ ምክንያቶችን መነሻ
እንደሚያደርጉ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድ ያሉ ደንቦችና ሕጎች እንዲጠበቁ
የተለያዩ ማህበራዊ ሽልማቶች እና ቅጣቶች አሉ፡፡ እነዚህ የማሕበረሰቡን ደንብ የጠበቀ
የሚከበርበት አለቃ እስከመሆን እንደሚያደርስ ከደንቡ ያፈነገጠ ደግሞ እንደየጥፋቱ አይነት
እንደሚቀጠና ካልታረመ ከአካባቢው እስከ መገለል እንደሚያደርስ ታውቋል፡፡ ማህበረሰቡ
ነውሮችን የሚፈጥረው ለአኗኗሩ መመሪያ እንዲሆነው፣ የልጆችን ስብዕና ለመቅረጽ፣
ላመነባቸውና ለሚገለገልበት ነገሮች የአጠቃቀም ስርአት ለማበጀት፣ በስነ ምግባር የታነፀ
ትውልድ ለመፍጠር በአጠቃላይ ፍላጎቶቹን ለማሟላት፣ የሚወደድ የሚጠላውን ለይቶ
ለማሳየት ነው፡፡ በመሆኑም ነውሮች የማህበረሰቡን ባህል እምነት፣ ታሪክ አስተሳሰብና
አመለካከት ዕውቀቱን የሚያሳውቁ ናቸው፡፡ ስለሆነም የነውሮች የመተላለፊያ መንገድ ቃላዊ
ስለሆነ የመረሳትና የመጥፋት እድላቸው የሰፋ ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች በጥናቱ ያልተካተቱ
ነውሮችን በመሰብሰብና በመሰነድ ለተተኪው ትውልድ ቢተላለፍ፣ መልካም ጎን ያላቸውን
ነውሮች ቢያስቀጥሉና አሁን ካለው የአኗኗር ሁኔታ ጋር የማይጣጣሙ ወይም አሉታዊ ጎን
ያላቸውን ነውሮች በሂደት ማሻሻያ ቢደረግባቸው የሚሉ የይሁንታ ሀሳቦችን በመጥቀስ ጥናቱ
ተጠናቋል፡፡