Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በሊቦ ከምከም ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዋሻ እንድርያስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚገኘውና በብራና ላይ በግእዝ ቋንቋ በተጻፈው የይዘት ትንተና በገድለ እንድርያስ ኢትዮጵያዊ ላይ በሚል ረእስ መሥራት ሲኾን ጥናታዊ ጽሑፉ በአራት ዋና ዋና ምዕራፎች ተከፋፍሎ የተደራጀ ነው፡፡
የዚህ ጥናት አቅራቢ ጥናታዊ ጽሑፉን ለመሥራት የመረጠውን ሥነ ዘዴ በተመለከተ ዓይነታዊ የጽሑፋት የይዘት መተንተኛ ሲኾን በውስጡ መሠረታዊ የመረጃ ምንጮች እና የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች ተካትተውበታል፡፡ በመኾኑም ለጥናቱ የተመረጠው የብራና ገድለ እንድርያስ ኢትዮጵያዊ በመጀመሪያ ደረጃ መረጃ ምንጭነት ጥቅም ላይ ሲውል ለኅትመት ካልበቃው መልክአ እንድርያስና መዝገበ ታሪካቸው በተጨማሪ ስለ ገድላት ምንነት፣ ጠቀሜታ፤ ስለ ገድሉና የገድሉ ባለቤት ማንነትና አገልግሎት የሚያብራሩ ልዩ ልዩ ሥነ ጽሑፎችን ከቃለ መጠይቆች ጋር በማጣመር በኹለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጭነት ተጠቅሟል፡፡ እንዲሁም የፎቶ ግራፍ ማንሻ ካሜራ ደግሞ በዋና የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያነት ጥቅም ላይ የዋለ ዘመናዊ መሳሪያ ነው፡፡ በመኾኑም እነዚህን ከላይ የተገለጹትን የጥናት ሥነ ዘዴ ዘርፎች በመጠቀም የሚከተሉትን ውጤቶች ለተደራስያን ማሳየት ችሏል፡፡
ገድሉ በግእዝ ቋንቋ ብቻ ተጽፈው ከሚገኙ ሀገር በቀል ሥነ ጽሑፎች መካከል አንዱ ከመኾኑ የተነሣ አብዛኛውን የይዘት ክፍል ወደ አማርኛ በመተርጐም የአማርኛ ተናጋሪዎች በቀላሉ እንዲረዱት የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ገድሉ ከአሁን በፊት በዘመናዊ መንገድ ያልተጠና ከመኾኑ አንጻር በይዘቱ ውሰጥ የተካተቱ ለአንባቢዎች ግልጽነት የጎደላቸውን ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ጉዳዮችን፤ ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን፤ የሰው፣ የታሪካዊ ቦታዎችንና የሌሎች እንስሳት ስሞችን ዓላማ፤ ከሌሎች ሥነ ጽሑፎች የተወሰዱ ሐሳቦችን፤ የዘይቤ አጠቃቀሞችን ከሙሉ ማብራሪያ ጋር ማሳየት ከመቻሉ በተጨማሪ የገድሉን ባለቤት ዜና ሕይወትና የገድሉን አጠቃላይ መገለጫዎች ለይቶ በማውጣት ማሳየት ችሏል፡፡