Abstract:
የዚህ ጥናት ዓላማ ራስን የመጠየቅ ብልሃት አንብቦ መረዳትን ለማጎልበት ያለው ሚና መመርመር ነበር፤ የጥናቱ ተሳታፊዎች በ2014 ዓ.ም ሆሞሻ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን የተከታተሉ በበርተኛ ቋንቋ አፋቸውን የፈቱ 169 የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ 82 የጥናቱ ተሳታፊ ተማሪዎች በቀላል ዕጣ ንሞና ተመርጠዋል፡፡ጥናቱ ፍትነት መሰል ሲሆን፣ ቅድመትምህርትና ድህረትምህርት ባለቁጥጥር ቡድን የተከተለ ነበር፡፡ የፍትነት ቡድን ተሳታፊዎች 41ተማሪዎች ራስን የመጠየቅ የማንበብ ብልሃት፣ የቁጥጥር ቡድኑ ተሳታፊዎች 41ተማሪዎች ደግሞ በተማሪ መጽሀፍና በመምህር መምሪያው ላይ በተመለከተው መሰረት ለአስራ አራት ክፍለጊዜያት አንብቦ መረዳትን እንዲማሩ በማድረግ ፍትነቱ ተተግብሯል። ቅድመትምህርትና ድህረትምህርት መረጃዎች አንብቦ የመረዳት ፈተና ከሁለቱም ቡድኖች ተሰብስበዋል፡፡ አንብቦ የመረዳት ችሎታ መረጃዎች በነፃ ናሙና ቲ-ቴስት ተፈትሿል፤ የነፃ ናሙና ቲ-ቴስትን መሰረት በማድረግ የድህረትምህርት መረጃዎች ውጤቶች እንዳመለከቱት፣አንብቦ በመረዳት ችሎታ አኳያ የተገኘው ውጤትም t(80) = 4.16, P<0.001 d=0.92 ሆኗል። በውጤቱ መሰረትም፣ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የፍትነቱ ቡድን በልጦ ጉልህ የስታትስቲክስ ልዩነት መኖሩን ታውቋል። ከዚያም ራስን የመጠቅ የማንበብ ብልሃት የተማሪዎችን አንብቦ የመረዳት ችሎታ ለማሳደግ ጉልህ አዎንታዊ ጠቀሜታ አለው፤ ከሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህ ድምዳሜ መሰረት መምህራን ራስን የመጠየቅ ብልሃት ለአንብቦ መረዳት ችሎታ ያለውን አስተዋጽኦ ተገንዝበው፤ ራስን የመጠየቅ ብልሃት ስልቶችን በቀጥታ ቢያስተምሩ፤ ተማሪዎች በሚያነቡበት ጊዜ ራስን የመጠየቅ ብልሃት ስልቶች ቅድሚያ ትኩረት እንዲኖራቸው ቢደረግ መልካም ነው በማለት የመፍትሔ ሃሳብ ተጠቁሟል፡፡