Abstract:
ይህ ጥናት ሚታዊ ጉዞና ፍለጋ በሐሽማል ረጅም ልቦለድ በሚል ርዕስ የተደረገ ጥናት ሲሆን ዋና አላማው በተመረጠው ልቦለድ ሚታዊ ጉዞና ፍለጋ እንዴት እንደተገለጸ ተንትኖ ማሳየት ነው፡፡ የጉዞ ምዕራፎች፣ የጉዞ አይነቶች፣ የፍለጋ ምዕራፎች፣ የፍለጋ አይነቶች፣ የሚታዊ ጉዞና ፍለጋ የመጨረሻ አላማ ምንነትን፣ ማሳየት የጥናቱ ዝርዝር አላማዎች ናቸው፡፡ አጥኚው እነዚህን አላማዎች ለማሳካት የተጠቀመው የመተንተኛ ዘዴ ደግሞ መዋቅራዊ የትንተና ስልት ነው፡፡ የመዋቅራዊ የትንተና ስልትን በመጠቀም በልቦለዱ ውስጥ ሚታዊ ጉዞና ፍለጋ እንዴት እንደተገለጹ ለማሳየት በልቦለዱ ውስጥ ትረካዎችን በማውጣት ተንትኗል፡፡ በልቦለዱ መለየት፣ መዝለቅና መመለስ የሚሉ ሚታዊ የጉዞ ምዕራፎች መኖራቸው ተብራርቷል፡፡ እንዲሁም ውስጣዊና ውጫዊ የጉዞ አይነቶች የተገለጹበት መንገድ ተተንትኗል፡፡ እንደ ጉዞ ሁሉ ሚታዊ ፍለጋው መለየት፣ መዝለቅና መመለስ የሚሉ የፍለጋ ምዕራፎችን የተከተለ መሆኑ በትንተና ተብራርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በልቦለዱ ውስጥ መሪው ገጸባህሪ ጠቢቡ ሖረ መሆናቸውን እና በጠቢቡ ሖረ አማካኝነት የፍለጋ ዓይነቶች የሚጨበጡና የማይጨበጡ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡ የህይወት ውሃ፣ ጸበልና ጥንታዊ የጥበብ መጽሃፍት ተጨባጭ የፍለጋ አይነቶች ሲሆኑ ጥበበኛ ትውልድ፣ ሀገር በቀል ጥበባት የመሳሰሉት ደግሞ በረቂቅነት የሚፈለጉ መሆናቸውን በትንተና ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ እንዲሁም በልቦለዱ የሚታዊ ጉዞና ፍለጋ የመጨረሻ አላማ ሀገር በቀል ጥንታዊ ጥበባትን መፈለግ መሆኑን በተለያዩ መሰረታዊ ማሳያዎች ተተንትኖ ተብራርቷል፡፡ በመጨረሻም ሐሽማል ልቦለድ በውስጡ ከሚታዊ ጭብጦች መካከል ጉዞና ፍለጋን በዋናነት የሚያሳይ ግሩም ሚታዊ ልቦለድ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡