Abstract:
ወለፈንዲነት የህይወትን ትርጉም አልባነት እና የሰው ልጅ ህይወት ወዳሻት የምትመራው
ተስፋ ቢስ ፍጥረት መሆኑን የሚያብራራ ፍልስፍና ነው፡፡የዚህ ጥናት ዓላማም ከህልውናዊነት
ጭብጦች ውስጥ አንዱ የሆነውን ወለፈንዲነት በሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ሁለት የተውኔት
ስራዎች ውስጥ አውጥቶ ማሳየት ነው፡፡ ጥናቱ ዓይነታዊ ጥናት በመሆኑ ቴክስቶችን በተገቢው
መልኩ በመፈተሽ የገላጭ ስልት እና የቴክስት ትንተናን በመጠቀም ተከናውኗል፡፡ በአማርኛ
ሥነ-ጽሑፍ አጥኚዋ ባደረገችው ምልከታ ወለፈንዲነትን እንደ ዋነኛ መመልከቻ መነፅር ወይም
መፈከሪያ ንድፈ ሃሳብ በመጠቀም የተደረገ ጥናት ማግኘት አልቻለችም፡፡ በጥናቱ ከወለፈንዲነት
መከሰቻ መንገዶች ውስጥ ተደጋግመው የሚነሱትን የህይወትን ትርጉም መሻት፣ የነፃነት፣
ባይተዋርነት፣ ቀቢፀ ተስፋ፣ አፈንጋጭ ቧልት እና ሳታየር እንዲሁም ቋንቋን ያለመግባባት
ምንጭ ማድረግ የሚሉት ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ በተመረጡት ተውኔቶች ውስጥ ያሉት ገፀ-
ባህሪያት ከህይወት ወለፈንዲነት ጋር ተግባብተው ለመኖር የሚያደርጉትን ጥረት እና ማግኘት
የቻሉትን ውጤት የሚያሳየንም ነው፡፡በተጨማሪም በሁለቱ ተውኔቶች ውስጥ የተከሰቱ
የወለፈንዲት መገለጫዎች እንዲሁም ጥቅም ላይ የዋሉበትን መንገድ አንድነት እና ልዩነትም
በሚገባ የተዳሰሰበት ጥናት ነው፡፡ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ ተውኔቶቹ በየዘመናቸው የነበረውን
ማህበራዊ እውነታ እና የሰው ልጅ ለዝብርቅርቅ ህይወት እንዲሁም ለምታሳድርበት ተፅእኖ
እየሰጠ ስላለው ምላሽ ተንፀባርቆበታል፡፡ በአጠቃላይ የጥናቱ ግኝት የህይወት ወለፈንዲነት
በተውኔቶቹ ዉስጥ በተለያዩ መንገዶች እንደ ተንፀባረቀባቸው ያሳያል፡፡በተጨማሪም ይህንን
ወለፈንዲነት በምን መንገድ ተቋቁመው ማለፍ እንደቻሉ ይተነትናል፡፡ ለዚህም የአለበርት
ካሙን ንድፈ ሃሳባዊ እሳቤዎች ተጠቅሟል፡፡