Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና አላማ በተማሪዎች የማንበብ ፍላጎትና በተሳታፊነትና በጥንቁቅነት
ሰብእናዎች መካከል ያለውን ተዛምዶ መመርመር ነው፡፡ ጥናቱ ተዛምዷዊ ስልት
ተከትሏል፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በምእራብ ኦሞ ዞን ባቹማ 2ኛ ደረጃ ትምህርትቤት፣
ጋቺት 2ኛ ደረጃ ትምህርትቤትና ጀሙ ህዳሴ 2ኛ ደረጃ ትምህርትቤት በ2013 ዓ.ም 9ኛ
ክፍል ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙ አጠቃላይ 463 ተማሪዎች መካከል
በእድል ሰጪ የእጣ ንሞና ዘዴ የተመረጡ 81 ተማሪዎች ናቸው፡፡ የጥናቱን አላማ ከግብ
ለማድረስ አስፈላጊ መረጃዎች በጽሁፍ መጠይቅ ተሰብስበዋል፡፡ የጽሁፍ መጠይቁ ለማንበብ
ፍላጎት መለኪያ 10 ጥያቄዎች፣ ለተሳታፊነት ሰብእና መለኪያ 10 ጥያቄዎችና
ለጥንቁቅነት ሰብእና መለኪያ 10 ጥያቄዎችን ይዟል፡፡ በተዛምዶውም ሁለቱም ነጻ
ተላውጦዎች ከጥገኛ ተላውጦው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፡፡ ይሁንና በጥናቱ ውጤት
መሰረት በማንበብ ፍላጎትና በተሳታፊነት ሰብእና መካከል ያለው (r= .05, p= .658)እና
በማንበብ ፍላጎትና በጥንቁቅነት ሰብእና መካከል ያለው (r= .13, p= .236) ተዛምዶ ጉልህ
አይደለም፡፡ ስለዚህ የተሳታፊነትም ሆነ የጥንቁቅነት ደረጃ መጨመርም ሆነ መቀነስ
ከማንበብ ፍላጎት መጨመር ወይም መቀነስ ጋር ያለው ግንኙነት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡
በመሆኑም የተሳፊነትም ሆነ የጥንቁቅነት ሰብእናዎች የተማሪዎችን የማንበብ ፍላጎት
ለመተንበይ የላቀ ድርሻ የላቸውም፡፡ ስለዚህ መምህራን የተሳታፊነትና የጥንቁቅነት
ሰብእናዎች ከተማሪዎች የማንበብ ፍላጎት ጋር ያላቸው ተዛምዶ ጉልህ አለመሆኑን
በመረዳት ለተማሪዎች የማንበብ ፍላጎት መጨመር በዚህ ጥናት ውስጥ ያልተካተቱ
ሰብእናዎች ወይም ሌሎች አበረታች ጉዳዮች ጉልህ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል ከግምት
ማስገባት እንዳለባቸው የጥናቱ ውጤት ይጠቁማል፡