Abstract:
የጥናቱ ዋና ዓላማ አማርኛ ቋንቋን በትብብራዊ መማር ብልሃት ማስተማር የተማሪዎችን የመጻፍ ችሎታ ለማጎልበት የሚኖረውን ሚና መመርመር ነው፡፡ ጥናቱ ባለሁለት ቡድን ቅድመ-ድህረትምህርት ፍትነትመሰል ንድፍን ተከትሎ የተጠና ሲሆን በተንታኝ የአቀራረብ ስልት ተካሂዷል። በፋግታ ለኮማ ወረዳ የሚገኙ የ2013 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ችጓሊና ፋግታ) ተማሪዎች የዚህ ጥናት ተሳታፊዎች ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ በአመቺ የንሞና ዘዴ ፋግታ የከፍተኛ ትምህርትና መሰናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በመምረጥ ጥናቱ ተካሂዷል፡፡ ለጥናቱ ውጤታማነትም በቅድመትምህርት መጻፍ ውጤታቸው ተመጣጣኝ የሆኑት የዘጠነኛ ክፍል ሁለት መማሪያ ክፍሎች (9ኛ G እና 9ኛ K) በዓላማ ተኮር የንሞና ዘዴ ተመርጠዋል፡፡ ለጥናቱ የተመረጡት ሁለት ክፍሎችም በተራ የእጣ ንሞና ዘዴ የሙከራ ቡድን (9ኛ G) እና የቁጥጥር ቡድን (9ኛ K) ሆነው ተለይተው መረጃ ሰጥተዋል፡፡ ለጥናቱ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን ለመሰብሰብም ቅድመትምህርትና ድህረትምህርት የመፃፍ ፈተናዎች አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡ በተገኘው ውጤት መሰረትም በቅድመትምህርት ፈተና የሙከራ ቡድን ተማሪዎች የመጻፍ አማካይ ውጤት 18.93 እንዲሁም የቁጥጥር ቡድን ተማሪዎች 19.21 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በመቀጠል የጥናቱ ተሳታፊዎች የድህረትምህርት የመጻፍ አማካይ ውጤት የሙከራ ቡድን 24.07፣ የቁጥጥር ቡድን 22.77 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህም አማርኛ ቋንቋን በትብብራዊ መማር ብልሃት ማስተማር የተማሪዎችን የመጻፍ ችሎታ በአማካይ በ 5.40 እንዲሁም በተለምዷዊው የማስተማር ስልት የጽህፈት ክሂልን ማስተማር በ 3.56 ከፍ እንደሚያደርግ (እንደሚያጎለብት) አመልክቷል፡፡ በድህረትምህርት የመጻፍ አማካይ ውጤት የተመዘገበው የጉልህነት ደረጃም (P<0.001) ከመቁረጫ ነጥቡ (0.05) አንሶ በመገኘቱ በሁለቱም ቡድኖች የተመዘገበው የድህረትምህርት የመጻፍ ውጤት ከቅድመትምህርት የፈተና ውጤት በስታቲስቲክስ ጉልህ ልዩነት እንዳላቸው እንዲሁም በትብብራዊ መማር ብልሃት ማስተማር በመደበኛው የማስተማር ስልት ከማስተማር የበለጠ የተማሪዎችን የመጻፍ ችሎታ ለማጎልበት እንደሚረዳ አረጋግጧል፡፡ በመጨረሻም አጥኚዋ የጥናቱን ግኝት መሰረት በማድረግ በአማርኛ ቋንቋ መምህራን፣ በተማሪዎች፣ በመርሀ ትምህርት ዝግጅት ባለሙያዎች እና በተመራማሪዎች ሊፈጸሙ የሚገባቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ጠቁማለች፡፡