Abstract:
ይህ ጥናት በአማራ ብሔራዊ ክልል በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በሰቆጣ፣ ድሃና
ጻግብጂ ወረዳዎች ዘንድ በሚከበረው የዋርዳሆዬ በዓል ቃል ግጥሞች የይዘት ትንተናና
ፋይዳ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። በዚህ አከባቢ እስካሁን ድረስ ወልደካህን ምስጋናው
(2003) የአስኮለልቻ በዓል በሚል በመጀመርያ ዲግሪ የአማርኛ ቃላዊ ግጥም የይዘት
ትንተና ላይ ካተኮረው ጥናት ውጪ በዋርዳሆዬ የቃል ግጥሞች በኽምጣጛም ሆነ በአማርኛ
ቃል ግጥሞች ዙሪያ የይዘት ትንተና ላይ ትኩረት አድርጎ ያጠና አጥኚ አላገኘሁም።
ጥናቱ ይዞ የተነሳው ዋና ዓላማ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ፣ ድሃናና ጻግብጂ
ዎረዳዎች በዋርዳሆዬ የክወና በዓል ወቅት በአፋዊ ግጥም አማካይነት ሲያስተላልፍበትና
ሲገልፅበት የቆየባቸውን የግጥም ይዘቶች በማሰባሰብና በማደራጀት ለመተንተንና ያለውን
ማህበራዊ፣ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ፋይዳ ለማብራራት ነው፡፡ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ፡-
ምልከታ፣ ቃለ መጠይቅ፣ ሰነድ ፍተሻና ተተኳሪ የቡድን ውይይት የመረጃ ማሰበሰቢያ
ዘዴዎችን በመጠቀም በቂ የሆኑ ቃል-ግጥሞች ተሰብስበዋል።
በዚሁ መሠረት በሰቆጣ ድሀናና ጻግብጂ ወረዳዎች በዋርዳሆዬ ክብረ በዓል ወቅት ከክበረ
በዓሉ ጅማሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሚካሄዱ ክዋኔዎች የሚገጠሙ የቃል ግጥሞችን
በየወገናቸው በመመደብ ተተንትነዋል፡፡ በዚህ ጥናት ማህበረሰቡ በቃል ግጥሞች
አማካይነት በቀጥታና በጎንዮሽ ሃሳቡን በመግለፅ ሲያስተምሩበት፣ ሲመክሩበት፣
ሲያዝናኑበት፣ ሲያስተላልፉበትና ባህላዊ ማንነትቱን ሲያስጠብቁበት መቆየቱን ማረጋገጥ
ተችሏል። ትንታኔ የተደረገው በዋናነት መረጃዎቹ ከተሰበሰቡበት አውድ አኳያ የይዘት
ትንተና የተጠቀመ ሲሆን የሥነ-ቃል ዓይነቶቹ በማህበረሰቡ ውስጥ ካለቸው ፋይዳ አንጻር
ደግሞ ተግባራዊ ትውርንና የክውና ትውርን መሠረት ያደረገ ነው። በእነዚህ የቃል
ግጥሞች አማካይነት የሚተላለፉ ቁምነገሮች እና የሚከወኑ ክዋኔዎች የማህበረሰቡን
ሁለንተናዊ መስተጋብር የማስተማር ሚና እንዳላቸው የጥናቱ ውጤት ያሳያል። በመሆኑም
ለወጣቱ ትውልድ ማስተማርያነት ማዋል እንደሚቻል በጥናቱ መደምደሚያ እና ይሁንታ
ውስጥ በዝርዝር ተገልጸዋል።