Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የመምህራን የጽሑፍ ምጋቤምላሾች አተገባበር ምን አንደሚመስል በማንኩሽ 2ኛ ደረጃ ትምህርትቤት በ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ተተኳሪነት መፈተሽ ነው፡፡ ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ጥናቱ ገላጭ ሀተታዊ የምርምር ስልትን ተከትሏል፡፡ ለዚህም በማንኩሽ ትምህርትቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን የሚያስተምሩ 2 የአማርኛ ቋንቋ መምህራንና ሁለቱ መምህራን ምጋቤምላሽ የሰጡባቸው የመጻፍ ተግባራት በጥናቱ ውስጥ ተካትተዋል፡፡ የተካተቱ ተግባራት በሁለት ዙር የተሰበሰቡ ሲሆን በመጀመሪያ ዙር ከመማሪያ ደብተራቸው ላይ የ31 ተማሪዎች መማሪያ ደብተር በግኝት ንሞና ተመርጠዋል፡፡ በሁለተኛው ዙር ደግሞ በተሰጣቸው የግል ሥራ ምጋቤምላሽ የተሰጠባቸው 31 ወረቀቶች በግኝት ንሞና ተመርጠዋል፡፡ በመሆኑም መረጃዎች የተሰበሰቡት ከ10ኛ ክፍል 62 ተማሪዎች ደብተሮችና የግል ሥራዎች በሰነድ ፍተሻ ሲሆን ለማመሳከሪያነት ደግሞ ከሁለቱ መምህራን በቃለመጠይቅ ነው፡፡ የተሰበሰቡ መረጃዎች በአብዛኛው በዓይነታዊ በገላጭ ሀተታዊ፣ በተወሰነ መጠን ደግሞ በመጠናዊ በመቶኛ ስሌት ተተንትነዋል፡፡ በትንታኔው ውጤትም መምህራን ከምጋቤምላሾች መካከል በዋናነት ገምጋሚ የምጋቤምላሽ ዓይነትን እንደሚጠቀሙ፣ መምህራኑ የጽሑፍ ምጋቤምላሽ በይበልጥ የቅርጽ ችግሮች ላይ የሚያተኩሩና በአብዛኛው ስህተቶችን መርጦ የማረም ስልትን እንደሚጠቀሙ በትንተናው ተረጋግጧል። በመጨረሻም ገምጋሚ የምጋቤምላሽ ዓይነት የመጻፍ ችሎታን ለማዳበር ያለው ፋይዳ አነስተኛ ስለሆነ የምጋቤምላሽ ዓይነቶችን ከጠቀሜታቸው አንጻር እየታዩ ቢሰጡ፤ ቅርጽተኮር የምጋቤምላሽ ትኩረት የመጻፍ ችሎታን በማዳበር በኩል የሚያመጣው ፋይዳ አነስተኛ መሆን አለመሆኑን በሙከራ ጥናት አረጋግጠው ሁለቱንም በቅንጅታዊ (የቅርጽና የይዘት ችግሮችን በጥምረት) መስጠት እንዲቻል ቢደረግ፤ ከጠቀሜታቸው አንጻር ስህተትን መርጦ የማረም ስልት ላይ ብቻ ከሚያተኩሩ ሌሎችንም ስልቶች እያጣጣሙ ቢጠቀሙ፤ የሚል አስተያየት በአጥኚው ተሰጥቷል።