Abstract:
ይህ ጥናት “ሞት በቅበላ ረጅም ልቦለድ፣ ነገረ ህላዌ ንባብ” በሚል ርዕስ የተጠና ነዉ፡፡ የዚህ
ጥናት አብይ ዓላማም ለምርምር በተመረጠዉ ልቦለድ ዉስጥ የነገረ ህላዌ፣ ሞት ጭብጥ
ተንትኖ ማቅረብ ነዉ፡፡ ይህን ጉዳይ ለማጥናት ምክንያት የሆነዉ ደግሞ ለምርምር
የተመረጠዉ ልቦለድ ራሱን ችሎ ሞትን ከነገረ ህላዌ ፍልስፍና አኳያ ጥናት አለመደረጉ፤
የነገረ ህላዌ ጭብጥ፣ ሞት በስፋት ስለሚንፀባረቁበትና በነገረ ህላዌ ሂስ ለማጥናት አመቺ
መሆኑ ነዉ፡፡ ይህ የህልዉናዊ ጭብጥ ከራሱ ከነገረ ህላዌ ፍልስፍና የሚመነጭ በመሆኑ ይህ
ፍልስፍና በመተንተኛ ስልትነት ጥቅም ላይ ዉሏል፡፡ በዚህ መሰረት ለምርምር በተመረጠዉ
ልቦለድ ዉስጥ ባሉ ገፀ ባህርያት ህልዉና ዉስጥ ተመላልሰዉ የተከሰቱ ዋና ዋና የሞት
ጭብጦች ማለትም ስነህይወታዊ ሞት፣ ራስ ግድያ፣ ጊዜውን የጠበቀ ሞት፣ ጊዜውን
ያልጠበቀ ሞት፣ በነገረ ህላዌ ፍልስፍና መተርጎሚያነት ተተንትነዉ ቀርበዋል፡፡ ከዚሁ ጋር
በተያያዘ በልቦለዱ የተገለፁት የነገረ ህላዌ ጭብጥ፣ ሞት የትኞቹ እንደሆኑ፣ እነዚህ ጭብጦች
መነሻ ምክንያታቸዉ ምን እንደሆና የቀረቡበትን ስልት እንዲሁም በገፀባህሪያቱ ህልዉና ላይ
ያስከተሉትን ተፅዕኖ በመተንተን ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ በዚህ መሰረት በዚህ ልቦለድ የቀረቡ
ሁሉም ገፀባህርያት ትርጉም ለማግኘት ይጠይቃሉ፤ ልዩ ልዩ ተግባራትን ይተገብራሉ፡፡
ትርጉም ሲያጡ ምርጫቸዉን ሞት ያደርጋሉ፡፡ በሚደርስባቸዉ የተለያዩ ተፅዕኖዎች
ምክንያት የሚኖሩበትን እዉነተኛ ዓለም ይጠላሉ፡፡ በህልም ዓለም መኖርን ይመርጣሉ፡፡
ሁሉም ባለትዳር ገጸ ባህሪያት በሚባል መልኩ የቅርብ የሚሉትን ሰዉ በመግደል
ራሳቸውንም በሞት ሲቀጡ ወይም ሲገድሉ ይታያል፡፡ በዚህ ጥናቱ በተሰራበት ልቦለድ
ያሉ ገጸ ባህሪያት ጊዜውን ያልጠበቀ ሟች ገጸ ባህሪያት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
በመሆኑም በልቦለዱ ውስጥ የተቀረፁ ገጸ ባህርያት ኑሮ ጊዜውን ካልጠበቀ ሞት
በተጨማሪ ገድሎ ሟች ናቸው ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁሉ በልቦለዱ
የተገለፁት በዚህ ጥናት የተለዩ ናቸዉ፡፡