Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ የሐሳብ ማደራጃ ብልሃቶች የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎችን
አንብቦ የመረዳት ችሎታ፣ የማንበብ ተነሳሽነትና በጥልቀት የማሰብ ችሎታ ለማሳደግ
ያላቸውን አስተዋጽዖ መመርመር ነው፡፡ የጥናቱ ተሳታፊ ተማሪዎች በባሕርዳር
ከተማ በዶናበርበር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት በ2014 ዓ.ም. በመማር ላይ
ከሚገኙ አምስት የሰባተኛ መማሪያ ክፍሎች መካከል በተራ የዕጣ ንሞና በተመረጡ
ሁለት የመማሪያ ክፍሎች የሚማሩ ነበሩ፡፡ ጥናቱ ቅድመትምህርት ፈተናና
ድኅረትምህርት ፈተና የቁጥጥር ቡድን ፍትነትመሰል ንድፍን የተከተለ ነበር፡፡
የፍትነቱ ቡድን ተሳታፊዎች (56 ተማሪዎች) በሐሳብ ማደራጃ ብልሃቶች አተገባበር
ዘዴ፣ የቁጥጥር ቡድን (56 ተማሪዎች) ደግሞ በተማሪ መጽሐፉ በቀረቡት
ተግባራት ብቻ አንብቦ መረዳት ትምህርት ለ12 ክፍለጊዜያት (12 ሳምንታት)
ተምረዋል፡፡ መጠናዊ መረጃዎችም ከሁለቱም ቡድኖች በአንብቦ መረዳት ፈተና፣
በማንበብ ተነሳሽነት የጽሑፍ መጠይቅና በጥልቀት የማሰብ ችሎታ መለኪያ ፈተና
ተሰብስበዋል፡፡ አይነታዊ መረጃዎች ደግሞ ከፍትነቱ ቡድን በቡድንተኮር ውይይት
ተሰብስበዋል፡፡ በቅድመትምህርትና በድኅረትምህርት የተሰበሰቡት መጠናዊ መረጃዎች
በአማካይ ውጤት፣ በልይይት ትንተና (ANOVA) እና የቤንፌሮኒ የጉልህነት
ማስተካከያ ስሌትን (p= .017) መሰረት በማድረግ በባለብዙ ተላውጦ ልይይት ትንተና
(MANOVA) የተተነተኑ ሲሆን፣ ከቡድንተኮር ውይይት የተገኙት መረጃዎች ደግሞ
በጭብጥ ትንተና ዘዴ (Thematic Analysis) ተተንትነዋል፡፡ የመጠናዊ መረጃዎች
ውጤቶች እንዳመለከቱት፣ በቅድመትምህርት ተመጣጣኝ አማካይ ውጤቶች
ያስመዘገቡት የፍትነቱና የቁጥጥሩ ቡድኖች በድኅረትምህርት የአንብቦ የመረዳት
ፈተና (p = .001, partial η2 = .160) በድኅረትምህርት የማንበብ ተነሳሽነት የጽሑፍ
መጠይቅ (p = .001, partial η2 = .644) እና በድኅረትምህርት በጥልቀት የማሰብ ችሎታ
ፈተና (p = .001, partial η2 = .361) የፍትነቱ ቡድን ተሳታፊዎች ከቁጥጥሩ ቡድን
ተሳታፊዎች በስታቲስቲክስ ጉልህ የሆነ የመሻሻል ልዩነት አሳይተዋል፡፡ የቡድንተኮር
ውይይት መረጃዎችም የመጠናዊ መረጃዎችን ውጤቶች የሚያጠናክሩ ሆነው
ተገኝተዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት የሐሳብ ማደራጃ ብልሃቶች የተማሪዎችን አንብቦ
የመረዳት ችሎታ፣ የማንበብ ተነሳሽነትና በጥልቀት የማሰብ ችሎታ ለማሳደግ ጉልህ
አዎንታዊ አስተዋጽዖ አላቸው፤ ከሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ የጥናቱን ግኝቶች
መነሻ በማድረግም ሥነትምህርታዊ የመፍትሄ ሐሳቦች ቀርበዋል፤ የወደፊት
የምርምር አቅጣጫዎችም ተጠቁመዋል፡፡