Abstract:
አዳም ረታ ‹‹ህጽናዊ›› ብሎ ከጠራው የስነ ጽሑፍ እሳቤው ጋር በርከት ያሉ መፃህፍቱን ለአንባቢያን እያደረሰ ይገኛል፡፡ አዳም በአንድ ጽሁፍ ውስጥ ያለን ታሪክ እንደገና እያሳደጉና ሌላ ፈርጅ እያወጡ ማሳደግ እንደሚቻል፤ ቀለል ተብሎ ይታይ የነበረን ታሪክ በሌላ ምዕራፍ ወይም መፅሐፍ፤ ወይም ደግሞ በሌላ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ መፃፍ የህጽናዊነት ማሳያ መሆኑን ይገልፃል፡፡
የህጽናዊነት ጽንሰ ሀሳብ ኢምበድድ ናራቲቭ፣ ሜታ ናራቲቭ፣ ራይዞም፣ ኢንተር ቴክስቹዋልና ኢንትራ ቴክስቹዋል ከሚባሉ ጽንሰ ሀሳቦች ጋር የሚያመሳስለው ጭብጥ አለ፡፡ ራይዞም በድርሰት ውስጥ አንዱ መስመር ከሌሎች መስመሮች ጋር የተያያዘ እና ማዕከልም ደርዝም የለለው ወሰን የለሽ የአፃፃፍ ስልት መከተሉ፤ ተካታች ታሪክ ተረክ (Embedded narrative) በታሪክ ውስጥ ያለን ታሪክ (story within story) የሚያሳይ የስነ ጽሑፍ ስልት መሆኑና በስልቱ ውስጥ በአንድ ታሪክ የመጣ ገፀ ባህርይ በሌላኛው ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን መልኩን ይዞ በድጋሚ እንዲመጣ የሚደረግበት የትረካ ስልት መሆኑ፤ ሜታ ናራቲቭ የተለያየ መጠን ያላቸው ታሪኮች ከአንድ ነጠላ ታሪክ ጋር ምክንያታዊ ሁነው ተቀርፀው፤ በቅደም ተከተል ተወስኖ የሚቀርብበት መሆኑ እንዲሁም ኢንተርቴክስቱዋሊቲ በአንድ ቴክስት ውስጥ የቴክስት ትርጉም መቅረጽና በተመሳሰይ ወይም ተዛማጅ ስነ ጽሑፋዊ ስራዎች መካከል ያለ ውስጣዊ ግንኙነት መፍጠር መሆኑ ከሕጽናዊነት ጋር ያዛምደዋል፡