Abstract:
የዚህ ጥናት አለማ፤ ራስመር የመማር ብልሃት የተማሪዎችን የአማርኛ ቋንቋ አንብቦ የመረዳት ችሎታን ለማጎልበት ያለውን ፋይዳ ለመመርመር ነበር፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ አስተዳደር በእውቀት ጮራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት በ2013 ዓ.ም በስምንት ምድቦች ከሚማሩ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በአመች የናሙና ዘዴ በተመረጡ ሁለት ክፍል ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ጥናቱ ቅድመትምህርት ፈተናና ድህረትምህርት ፈተና ባለቁጥጥር ቡድን ፍትነትመሰል የምርምር ስልት የተከተለ ነበር፡፡ የፍትነቱ ቡድን ተሳታፊዎች (42 ተማሪዎች) በራስመር የመማር ብልት፤ የቁጥጥሩ ቡድን ተሳታፊዎች (41 ተማሪዎች) ደግሞ በመደበኛው የመምህር መምሪያና የተማሪ መጽሐፍ መሰረት አንባቦ የመረዳት ትምህርት ለ8 ክፍለጊዜያት (ለ6 ሳምንታት) ተምረዋል፡፡ መረጃዎችም በቅድመትምህርትና በድህረትምህርት አንብቦ የመረዳት ፈተና ተሰብስበዋል፡፡ እዲሁም በሁለቱ ቡድኖች አማካይ ውጤቶች መካከል የጎላ ልዩነት መኖር አለመኖሩ በባዕድ ናሙና ቲ-ቴስት (independent samples t-test) በመጠቀም ተተንትነዋል፡፡ በሁለቱ አማካይ ውጤቶች መካከል ጉልህ ልዩነት መኖር አለመኖሩን ለማወቅ መረጃው በባዕድ ናሙና ቲ-ቴስት ፍተሻ ተሰልቶ፣ ውጤቱ (t(81)= .299፣ P=0.765) ሆኗል፤ ይህም በቡድኖቹ ድህረትምህርት የአንብቦ መረዳት ችሎታ አማካይ ውጤቶች መካከል በስታትስቲክስ ጉልህ ልዩነት እንደሌለው አሳይቷል፡፡ ከዚህ ውጤት በመነሳትም በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በራስመር የመማር ብልሃቶች ታግዞ ማንበብን መማር በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ጉልህ የሆነ መሻሻል አያሳይም ከሚል መደምደሚያ ላይ ተደርሷል፡፡ በመሆኑም ተጨማሪ ጥናት ቢደረግ የሚል አስተያየትም ተጠቁሟል