Abstract:
ይህ ጥናት ሴትነት በገድለ ወለተ ጴጥሮስ እና በገድለ ክርስቶስ ሠምራ እንዴት እንደተሳለ
የሚፈትሽ ሲሆን ሴትነታቸው ቅድስናቸውን መሸፈን አለመሸፈኑንም ተመልክቷል፡፡
በተጨማሪም የተጋዳልያኑን (ዋና ገጸ ባሕርያቱን) ጉዞም ዳስሷል፡፡ ይህ ጥናት ሴትነትን
ለመመልከት አንስታይ ትወራና ሂስ የተጠቀመ ሲሆን መጻሕፍቱ ገድላት እንደመሆናቸው እና
የገጸ ባሕርያቱን ጉዞ ለመመልከት ሚታዊ ትወራን ተጠቀሟል፡፡ ይህ ጥናት ዓይነታዊ ዘዴን
የተከተለ ሲሆን በዓላማዊ ናሙና አመራረጥ ዘዴ ገድላቱ ተመርጠዋል፡፡ ለመረጃ መሰብሰቢያም
የተጠቀምኩት ሰነድ ፍተሻ ዘዴን ነው፡፡ ሰላማዊት (2006 እ.ኤ.አ.) እና አራጌ (2001ዓ.ም)
ከደረሱበት (ከጠቀሱት) በተቃራኒ በዚህ ጥናት ሴትነት በገድላቱ ውስጥ ለቆራጥነት፣ ለዓላማ
ጽናት፣ ለሐሳብ ልዕልና፣ ለዕርቅ፣ ለፍቅር፣ ለአንድነት፣ ለጀግንነት፣ ለእኩልነት እና ለመሪነት
ምሳሌ ሆኖ እንደተሳለ መመልከት ችያለሁ፡፡ በተለይም ሴቶች ከወንዶች እንደማያንሱ በተግባር
ለማሳየት ተመራጭ መጻሕፍት ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ለዚህም ምስክር የሚሆኑ ተአምራትን
ተጋዳልያኑ በገድላቸው ውስጥ ሲፈጽሙ ይታያል፡፡ ለምሳሌ የታመመ ማዳን፣ የሞተ
ማስነሣት፣ ኃጢኣተኛን ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ፣ ከመላእክት ጋር መነጋገር፣ ከሰማይ
የወረደ ኅብስት መብላት መቻል፣ ነፋሳትን መገሰጽ፣ እገዚአብሔርን ማነጋገር መቻል
የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ወንዶቹ ቅዱሳን የሚፈጽሟቸው ተአምራትም ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡፡
በመሆኑም ሴትነታቸው ቅድስናቸውን እንዳልሸፈነው እና የክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮም
መንፈሳዊነት ወይም ቅድስና የሴት የወንድ እንደማይል ለማስተማር ብቁ መሳሪያዎች እንደሆኑ
ማሳየት ችያለሁ፡፡ በተጨማሪም ገድላቱን በሚት ዓይን ስናያቸው የተጋዳሊውን ጉዞ በደንብ
ማሳየት ይችላሉ፡፡ በዚህም የገድል ጥሪን የመጀመሪያውን ቅጽር መዝለቅ፣ የልዕለ ተፍጥሮ
ረድኤት፣ የአሳ ነባሪ ከርስን፣ እና በረከት ይዞ መመለስን ገድላቱ በጉልህ ያሳያሉ፡