Abstract:
ይህ ጥናት የታሪክና የገጸ ባህርያት በይነአሃዳዊነት በተመረጡ የአዳም ረታ ስራዎች በሚል
ርዕስ የቀረበ ነው፡፡ ለጥናት የተመረጡት እቴሜቴ ሎሚ ሽታ (2005)ና መረቅ (2007)
የተሰኙት ሥራዎች ሲሆኑ እነዚህ ድርሰቶች ቀድመው ከመጡ ድርሰቶች ማለትም ከፍቅር
እስከ መቃብር (1999)፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ (1962)ና ከትውፊታዊ የልጆች ቃላዊ ጨዋታ ጋር
ያላቸውን በይነአሃዳዊ ግንኙነት መተንተን ሲሆን ዋና ዓላማውም የተመረጡ የአዳም ረታ
ስራዎች ከሌሎች ድርሰቶች ታሪክና ገጸ ባኅርያትን እንዴት እንደወሰዱ ማሳየት ነው፡፡
ለጥናት የመረጥኋቸውን ድርሰቶች በወጉ ለመተንተን የተጠቀምኩት በይነአሀዳዊነት የተባለውን
ቲወሪ ሲሆን የመተንተኛ ስልቱ ደግሞ ፍካሬ ነው፡፡ በዚህም በድርሰቶቹ ውስጥ ያለውን ግንኙነት
ለመመርመር የበይነአሃዳዊ አይነቶችን፣ ደረጃዎችንና ስልቶችን ተጠቅሜ በለስና መጽሃፍ ቅዱስ፣
ትውፊታዊ የልጆች ጨዋታና እቴሜቴ ሎሚ ሽታ፣ መረቅና ፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ ያሉት
አጫጭር ታሪኮችን መመሳሰል ማሳየት ነው፡፡
እቴሜቴ ሎሚ ሽታ (2005) ውስጥ የምናገኘው “በለስ” የተሰኘው ኖቬላ ድርሰት ከመጽሐፍ
ቅዱስ (1962) ኦሪት ዘፍጥረት ታሪክ ጋር፤ “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” የተሰኘው ተረክ
ከትውፊታዊ የልጆች ጨዋታ ጋር፤ መረቅ (2007) በተሰኘው ዘለግ ያሉ የኣጫጭር ልቦለዶች
ሰብስብ ውስጥ ደግሞ “ሁረቱ አላዛር” የተሰኘው ትረካ ከፍቅር እስከ መቃብር (1999) ጋር
ያላቸውን የታሪክና የገጸ ባህርያት አንድነት በጥናቴ አረጋግጫለሁ፡፡
በአጠቃላይ በአዳም ረታ የጠመረጡ ሥራዎች ውስጥ የማነሳው የታሪክና የገጸ ባህርያት
በይነአሃዳዊ ግንኙነት ድርሰቶቹ ቀድመው ከወጡ ሌላ ሥራዎች በአንድም በሌላ መንገድ እንደ
አዲስ ተደግመው መምጣታቸውን በቲወሪ አዳብሬ፤ መረጃና ማስረጃ በማቅረብ ለማሳየት
ሞክሪያለሁ፡፡ በዚህ ምክንያትም ድርሰቶቹ ውስጥ የታሪክና የገጸ ባህርያት በይነአሃዳዊነት
ወይም መመሳሰል የጥናቴ ግኝት ነው፡፡