Abstract:
ዚህ ጥናት ዓላማ አዕምሯዊ የማንበብ ብልሃት የተማሪዎችን አንብቦ የመረዳት ችሎታ
የማጎልበት ሚና መፈተሽ ነው፡፡ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ፍትነት መሰል (Quasi-
experimental) የጥናት ንድፍ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ
ከተማ አስተዳደር በየካ ክፍለከተማ ወረዳ 11 ደጃዝማች ወንድይራድ መሰናዶ ትምህርትቤት
በ2013 ዓ.ም 11ኛ ክፍል ሲማሩ ከነበሩ በ22 የመማሪያ ክፍል ከሚገኙ 990 ተማሪዎች
መካከል በቀላል እጣ ንሞና ዘዴ በተመረጡ ሁለት መማሪያ ክፍሎች የተገኙ 90 ተማሪዎች
ናቸው፡፡ በመሆኑም በአዕምሯዊ የማንበብ ብልሃት በመታገዝ ማንበብን የሚማር ቡድንና
አሁን ባለው መንገድ ማንበብን የሚማር ቡድን በማድረግ አንብቦ የመረዳት ትምህርትን
ለተከታታይ 8 ሳምንታት በሳምንት ለሦስት ክፍለጊዜ ያህል ማንበብን ተምረዋል፡፡ ከጥናቱ
ተሳታፊዎችም ቅድመትምህርትና ድህረትምህርት አንብቦ የመረዳት ችሎታ በፈተና
አማካይነት መረጃው ተሰብስቧል፡፡ የተሰበሰበው መረጃም በአማካይ ውጤት፣ በመደበኛ
ልይይትና በባዕድ ናሙና ቲ-ቴስት ተሰልቶ ተተንትኗል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንዳመለከተውም
አዕምሯዊ የማንበብ ብልሃትን ሳይጠቀሙ አሁን ባለው ማንበብን ከተማሩት የቁጥጥር ቡድን
ተማሪዎች ይልቅ በአዕምሯዊ የማንበብ ብልሃት በመታገዝ ማንበብን የተማሩት የሙከራ
ቡድን ተማሪዎች አንብቦ የመረዳት ችሎታቸው ጉልህ ልዩነቱ (t(88)=2.64፣ የተጽዕኖ
ደረጃው (effect size) መካከለኛ (eta squared = 0.104) በመሆን መሻሻል አሳይቶ
ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም ከጥናቱ ውጤት በመነሳት በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት አዕምሯዊ
የማንበብ ብልሃትን ተጠቅሞ ማንበብን መማር የተማሪዎችን አንብቦ የመረዳት ችሎታ
ያጎለብታል ከሚለው ድምዳሜ ተደርሷል፡፡ ስለሆነም መምህራን ማንበብን በሚያስተምሩበት
ወቅት አዕምሯዊ የማንበብ ብልሃቶችን ተጠቅመው ለተማሪዎች ስለብልሃቱ ተግባራዊ ግንዛቤ
ማስጨበጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ጥናት ያልተዳሰሱ ጉዳዮችና የወደፊት
የምርምር አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡