Abstract:
ይህ ጥናት “ሥነልቦናዊ የመከላከያ ዘዴዎች በሐሰተኛው፤በእምነት ሥም ረጅም ልቦለድ ውስጥ”
በሚል ርዕስ የተካሄደ ነው፡፡ ጥናቱ በተመረጠው ቴክስት ውስጥ ገጸባህሪያት በተለያዩ ምክንያቶች
የተጠቀሟቸውን ሥነልቦናዊ የመከላከያ ዘዴዎች በመለየት እንዴት እንደተጠቀሙት የፍሮይዳዊ
የሥነልቦና ጽንሰ ሀሳቦች መነሻ በማድረግ በትንተና ማሳየት አላማ አድርጎ የተከናወነ ነው፡፡ ጥናቱ
ከአይነታዊ የጥናት ዘዴዎች መካከል ንጥል ጥናትን በመጠቀም ቴክስት ትንተናው ተካሂዷል፡፡
በጥናቱ በታሪኩ ከተሳሉት ዋና ገጸባህሪያት ወስጥ አላዛር፣ናትራ፣ቡልቡላና ኤልሳቤጥ
ከሚያጋጥሟቸው ችግሮችና የህይወት ውጣ ውረዶች ለመውጣት ከሥነልቦናዊ የመከላከያ ዘዴዎች
ውስጥ ወደኋላ መመለስ፣መራቅ፣ጭቆና፣መካድና ማላከክን ተጠቅመዋል፡፡ ገጸባህሪያት የሥነልቦናዊ
መከላከያ ዘዴዎችን ሲጠቀሙ በኢ-ንቁ አዕምሮ የተቀመጡ የጥፋተኝነት ስሜቶች፣ ትውስታዎች፣
ፍርሃት፣ከዚህ በፊት የገጠሙን አሰቃቂ ሁኔታዎች፣መጥፎ ገጠመኞች፣ እንዲመለሱ
የማንፈልጋቸው ጭንቀቶችንና ያልተፈቱ ጉዳዮች በማውጣት የሰብዕና መዋውሮችን (ኢጎ፣ኢድና
ሱፐርኢጎ) እንደሚያጋጥሟቸው ችግር በአግባቡ ተጠቅዋል፡፡ በታሪኩ ውስጥ ያሉ ዋና ገጸባህሪያት
ሥነልቦናዊ የመከላከያ ዘዴዎችን አብዝተው የመጠቀም ሁኔታ ያሳዩት በልጅነት አስተዳደግ ችግር
ምክንያት፣በህይወት አጋጣሚ በተፈጠሩ መጥፎ ክስተቶች እና ኢጎን ተጠቅሞ በደመነፍሳዊ
ተነሳሽነት ፍላጎትን ለማርካት በማሰብ በተሰራ ስህተት መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ
ውስጥ ያለፉ ገጸባህሪያት ፍቅርን ፈርቶ የመሸሽ ሁኔታ ውስጥ መግባት፤ በጭንቀት
በማይፈልጉት ስራ እንዲዘልቁ መገደድ፤ በቅናት መብሰልሰል እንዲሁም ወደ ቀድሞው ህይወት
መመለስ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በአጠቃላይ ከችግር ለመውጣት በማሰብ የተለያዩ ሥነልቦናዊ
የመከላከያ ዘዴዎችን አብዝተው ቢጠቀሙም ከችግር መውጣት እንዳልቻሉ በትንተናው
ተመላክቷል፡፡