Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና አላማ የተማሪዎች የማንበብ ብልሃቶች አጠቃቀምና የማንበብ ተነሳሽነት
ተዛምዶን መመርመር ነው፡፡ ጥናቱ ተዛምዷዊ ስልት ተከትሏል፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በሲዳማ
ክልል በይርጋለም ከተማ አስተዳደር በራስደስታ ዳምጠው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት በ2013
ዓ.ም በ10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል በእድል
ሰጪ የንሞና ዘዴ የተመረጡ 50 ተማሪዎች ናቸው፡፡ የጥናቱን አላማ ከግብ ለማድረስ በሁለት
ዓይነት የጽሁፍ መጠይቅ አስፈላጊ መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ መረጃዎቹም
በ``SPSS``ተተንትነዋል፡፡ በተማሪዎች የማንበብ ብልሃቶችና በማንበብ ተነሳሽነት መካከል
ያለው ተዛምዶ ምን ያህል እንደሆነ ለመመርመር ደግሞ የፒርሰን ተዛምዶ መወሰኛ ቀመርና
ኅብረ ድኅረት ተዛምዶ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ የማንበብ ብልሃት አይነቶች አጠቃቀምና በማንበብ
ተነሳሽነት መካከል ጉልህ የሆነ አስተማማኝነት እንዳለ የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡እንዲሁም
ጥቅል የማንበብ ብልሃቶች ከማንበብ ተነሳሽነት ጋር ጉልህና አዎንታዊ ተዛምዶ እንደለ
ታውቋል፡፡ (r=.418 p=.003) ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተዛምዶውም ሁሉም ነጻ ተላውጦዎች ከጥገኛ
ተላውጦው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፡፡ ከማንበብ ብልሃት አይነቶች ውስጥ ከማንበብ
ተነሳሽነት ጋር ጉልህ አንዎታዊ ተዛምዶ ያለው ማህበረስሜታዊ ብልሃት ብቻ መሆኑ
የ(r=.651, p=.000) ውጤት አሳይቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የትኛው የማንበብ ብልሃት
የማንበብ ተነሳሽነትን ከመተንበይ ረገድ የላቀ ድርሻ አለው የሚለውን ለመለየት በተደረገ ኅብረ
ድኅረት ትንተና ፍተሻ መሰረት ማህበረስሜታዊ የማንበብ ብልሃት ብቻ አዎንታዊና የላቀ
የመተንበይ ድርሻ ያለው ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ውጤቱም (β.651,t=5.940,p=.000) ነው፡፡
በመሆኑም መምህራን በክፍል ውስጥ የአንብቦ መረዳት ትምህርትን በሚያስተምሩበት ጊዜ
የተማሪዎችን የማንበብ ብልሃት አይነቶች መጠቀምና ተማሪዎች የማንበብ ተነሳሽነት
እንዲኖራቸው ማህበረስሜታዊ የማንበብ ብልሃት ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑን ከግምት
ውስጥ ሊያስገቡ እንደሚገባ አጥኚው ጠቁማል፡፡