Abstract:
የዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ርእስ ‹‹ፍላጎት በቃል ኪዳን ረጅም ልቦለድ ውስጥ፤ከLacanian የፍካሬልቦና ትችት አንጻር›› የሚል ነው፡፡ የጥናቱ ዐብይ ዓላማ ‹‹በቃል ኪዳን›› ረጅም ልቦለድ ውስጥ
የዋና ገጸ-ባህርያትን ፍላጎቶችን እና የፍላጎት ምንጮችን ማሳየት ነው፡፡ የጥናቱ ወሰን ደግሞ
‹‹በቃል-ኪዳን›› ረጅም ልቦለድ እና በLacanian, ‹‹ፍላጎት››፣ ‹‹የባይተዋርነት›› እና ‹‹ፋለስ››
የሚሉትን ጽንሰ-ሐሳቦች በመመርመር ላይ የተገደበ ነው፡፡ ይህ ጥናት የሥነ-ጽሑፋዊ ጥናት
(ሂስ) ስለሆነ አይነታዊ የምርምር ዘዴን እና ቴክስታዊ የትንተና ሥልትን የተከተለ ነው፡፡
መረጃ ለመሠብሠብም ቀዳማይ እና ካልዓይ የመረጃ ምንጮች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ከመረጃ
ትንተናው ዋና ዋና ግኝቶች መካከል የመጀመሪያው፣ ገጸ-ባህርያቱ ፍላጎታቸውን በሌላ እና ሌላ
ሥልት ለማሟላት ሲጥሩ ታይቷል፡፡ ሁለተኛው፣የልቦለዱ ገጸ-ባህርያት ፍላጎታቸውን
ለማሟላት በሚያደርጉት ጥረት የእኔ እንጂ የሌላው የሚለው ግድ ስለማይላቸው የሌላነት
ስሜት ተንጸባርቆባቸዋል፡፡ ሦስተኛው፣የሴት ገጸ-ባህርያቶች ፍላጎት በማኅበረ-ባህላዊ ሕግ
ተጽእኖ ሥር የወደቀ ነው፡፡ አራተኛው፣ የትንተና ውጤት በእውናዊ ሥርዓት ውስጥ የገጸባህርያቱ ፍላጎት የተደናቀፈበትን ሁኔታ የሚያሣይ ነው፡፡ በመሆኑም ገጸ-ባህርያቱ ኢ-ንቁ
ፍላጎት እጦታቸውን በጽሑፍ (ስንኝ በመቋጠር እና ደብዳቤ በመጻፍ)፣ በሕልም፣ በቅዥት፣
በቁጣ እና በስካር ለመግለጽ ሲጥሩ ይታያሉ፡፡ ቋንቋ የፍላጎት ማሟያ እና ለእጦት ምክንያት
እንደሚሆን በትንተናው ታይቷል፡፡ በስድብ ቃላት ፋለስን መነጠቅ እንዳለም ትንተናው
ያሣያል፡፡ የልቦለዱ ገጸ-ባህርያት የሚያሳዩት ኢ-ንቁ የሆነ የፍቅር፣የገንዘብ፣የሞት እና የበቀል
ፍላጎት ለፍርሃት፣ለጭንቀት፣ለስጋት፣ለስቃይ እና ለእጦት እንደዳረጋቸው ትንተናው
ያመላክታል፡፡ የተወሰኑት ዋና ዋና ገጸ-ባህርያት ለሚገጥማቸው ከባድ እጦት፣የአእምሮ ሕመም
እንዲሁም ሞት ዋናው መንስኤም ሊሳኩ ያልቻሉት ኢ-ንቁ ፍላጎቶች ናቸው፡፡ ይህም የሰው
ልጆች ፍላጎት በእጦት እና በስቃይ የተሞላ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡