Abstract:
አኅጽሮተጥናት
የዚህ ጥናት ዓላማ የአማራጭ ምዘናዎችን የተማሪዎችን ድርሰት የመጻፍ ችሎታ የማሻሻል ሚና መመርመር ነበር፡፡ ዓላማውን ከግብ ለማድረስም በሁለት ቡድኖችና በሁለት የትግበራ ዙሮች የቀረበ የአመጣጣኝ ንድፍ (Counterbalanced design) ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በጥናቱ ትግበራ ሂደት በ2010 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሑፍ-ዐማርኛ ትምህርትክፍል ይማሩ የነበሩ 49 የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ከተሳታፊዎች የተሰበሰቡት መረጃዎች በሁለት የትግበራ ወቅቶች ከቀረቡት አጠቃላይ ድርሰት የመጻፍ ችሎታ ፈተናዎች፣ ድርሰት የመጻፍ ንዑሳን ችሎታዎች ምዘናዎች፣ ድርሰት የመጻፍ ሂደታዊ ዕድገት መገምገሚያዎች፣ የተማሪዎች ናሙና ድርሰቶችና የፖርቲፎልዮ ማስታወሻዎች ናቸው፡፡ የተገኙት መረጃዎችም የየመተንተኛ ስልቶቻቸው እሙኖች በገላጭ ስታትስቲክስ ከተፈተሹ በኋላ፣ በፍትነትና በቁጥጥር ቡድኖች መካከል ያለውን ልዩነት ለመመርመር፣ የአጠቃላይ ድርሰት የመጻፍ ችሎታ ፈተናዎች አማካይ ውጤቶች በባዕድ ናሙና ቲ-ቴስትና በአበር ልይይት፣ ድርሰት የመጻፍ ንዑሳን ችሎታዎች በባለብዙ ተላውጦ ልይይትና አበር ልይይት፣ ድርሰት መጻፍን በመማር ረገድ ሂደታዊ ዕድገቱን ለመፈተሽ በዳግም ልኬትና ቅይጥ አበር ልይይት ተሰልተው ተተንትነዋል፡፡ እንዲሁም ከተማሪዎች ናሙና ድርሰቶችና የፖርቲፎልዮ ማስታወሻዎች የተገኙት ዓይነታዊ መረጃዎች ከመጠናዊ መረጃዎቹ ጋር እየተቀናጁ ተተንትነዋል፡፡ በተገኙት ውጤቶች መሠረትም፣ በሁለቱም የትግበራ ወቅቶች የአጠቃላይ ድርሰት የመጻፍ ችሎታ፣ የመጻፍ ንዑሳን ችሎታዎችና የመጻፍ ሂደታዊ ዕድገት አማካይ ውጤቶች የፍትነት ቡድን ከቁጥጥር ቡድን አማካይ ውጤቶች ተሽለውና ጉልህ ( p < .05) ልዩነት ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በተጨማሪም የመጠናዊ መረጃዎቹ ውጤቶች የዓይነታዊ መረጃዎች ድጋፍም አግኝተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከመጠናዊና ከዓይነታዊ መረጃዎች የተገኙት ውጤቶች የአማራጭ ምዘናዎች የተማሪዎችን ድርሰት የመጻፍ ችሎታ የማሻሻል ሚና እንዳላቸው አሳይተዋል፡፡ የጥናቱ አንድምታም ድርሰት መጻፍን በመማር ሂደት የአማራጭ ምዘናዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ያመላክታል፡፡ በመሆኑም፣ ድርሰት የመጻፍ ትምህርት ይዘቶችና ተግባራት ከአማራጭ ምዘናዎች ጋር አዋህዶ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡