Abstract:
አኅጽሮተ ጥናት
ጥናቱ አላማ አድርጎ የተነሳው የተማሪዎች አውድ ተኮር እና ተንታኝ የመማር ስልቶች
በአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ያላቸውን ተጽእኖ መመርመር ሲሆን ጥናቱ ገላጭ ምርምርና
ንጽጽራዊ ንድፍን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ
መንግስት በደቡብ ጐንደር ዞን አስተዳደር በደብረታቦር ከተማ በሚገኙ በዳግማዊ ቴዎድሮስ
ከፍተኛ ትምህርት ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርትቤትና በእቴጌ ጣይቱ አጠቃላይ ከፍተኛ
ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርትቤት በ2010 ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ባሉ
የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ ነው፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች አመራረጥም በስርአታዊ እጣ
ናሙና (systematic random sanpling) ዘዴ አመራረጥ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ስርአታዊ እጣ
የናሙና አመራረጥ ዘዴን በመከተል ካሉት 2,080 ተማሪዎች 109 ተማሪዎች የጥናቱ
ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡ ለመረጃ መሰብሰቢያነትም የዎንግ (2015) ተሻሽሎ የተወሰደ የጽኁፍ
መጠይቅ እና የአንብቦ መረዳት ፈተና ስራ ላይ የዋሉ ሲሆን የተሰበሰቡት መረጃዎችም
በገላጭ እና ተንባይ ስታትስቲክስ ተሰልተዋል፡፡ በመረጃው ትንተና መሰረትም በተማሪዎች
ሁለት የመማር ስልቶች መካከል ጉልህ ልዩነት /P<0.05/ የታዬ ሲሆን ለልዩነቱም
የተንታኝ የመማር ስልት ከአውድ ተኮር የመማር ስልት ይበልጥ አውንታዊ ተጽኖ መኖሩ
ምክንያት ሆኗል፡፡ በአብዛኛው የተማሪዎች የመማር ስልት ወደ ተንታኝ ያመዘነ መሆኑን
አመላክቷል፡፡ የተማሪዎች የአውዳዊ የመማር ስልት በአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ
የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመፈተሽ በተደረገው ትንተና የአውድ ተኮር ስልት በአንብቦ
መረዳት ችሎታ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ፡፡ ይሁን እንጂ፣በዚህ ጥናት ተንታኝ
የመማር ስልት በአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ከፍተኛ አውንታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር
መረዳት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ፣ በጥናቱ ውጤት መሰረት የመማር ማስተማሩ ተግባር
ሲከናወን መምህራን የመማር ማስተማሩን ተግባር ከተማሪዎች የመማር ስልትና የአንብቦ
መረዳት ችሎታ ጋር የተጣጣመ ቢያደርጉ፤ የመማር ስልት ምርጫቸውና የአንብቦመረዳት
ችሎታቸውን ያጣጣሙ ተግባራት ቢመቻቹላቸው፤ መርሃ ትምህርሲቀረጽ የተማሪዎች
የመማር ስልትና የአንብቦ መረዳት ችሎታን ግምት ውስጥ በማስገባት ስርአተ ትምህርቱን
ቢያሻሽሉት የሚሉት አስተያየቶች በአጥኝው ተሰጥተዋል፡፡