Abstract:
አህጽሮተ-ጥናት (Abstract)
የጥናቱ ዋና ዓላማ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮችን በመጠቀም መጻፍን
መማር የተማሪዎችን የመጻፍ ችሎታ ለማሻሻል የሚኖረውን ሚና መፈተሽ ነው፡፡ ዓላማውን
ለማሳካትም ፍትነትመሰል(Quasi-experiment) የጥናት ንድፍ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ የጥናቱ
ተሳታፊዎች በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬ ከተማ አስተዳደር በአጣዬ የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶና
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት በ2010 ዓ.ም በዘጠነኛ ክፍል ሲማሩ ከነበሩ በ17 መማሪያ ክፍል
ከሚገኙ1015 ተማሪዎች መካከል በተራ እጣ ንሞና ዘዴ በተመረጡ ሁለት መማሪያ ክፍሎች
የተገኙ 92 ተማሪዎች ናቸው፡፡በመሆኑም በሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮች መጻፍን የሚማር ቡድንና
ያለሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮች በተለመደው መንገድ መጻፍን የሚማር ቡድን በማድረግ የመጻፍ
ክሂል ትምህርትን በ8 ሳምንታት ለ17 ክፍለ ጊዜያት ተምረዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹም
ቅድመትምህርትና ድህረትምህርት የመጻፍ ችሎታ በፈተና፣ ቅድመትምህርትና ድህረትምህርት
የመጻፍ ተነሳሽነት በመጠይቅ አማካይነት ተለክተው መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ መረጃዎቹም
በአማካይ ውጤት፣ በመደበኛ ልይይት፣ በባዕድ ናሙና ቲ-ቴስት ተሰልተው ተተንትነዋል፡፡
የጥናቱ ግኝቶች እንዳመላከቱትም ያለሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮቹ በተለመደው መንገድ መጻፍን
ከተማሩት ተማሪዎች ይልቅ የሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮችን በመጠቀም መጻፍን የተማሩት በመጻፍ
ችሎታቸው ጉልህ (t(90)= 4.974፣ P=0.000) መሻሻል ከማሳየታቸው ባለፈ የተጽዕኖ ደረጃው
(effect size) ከፍተኛ ሆኖ (eta squared = 0.22) ተገኝቷል፡፡ በተመሳሳይ በመጻፍ
ተነሳሽነታቸውም በሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮች የተማሩት ተማሪዎች ጉልህ (t(90)= 2.742፣
P=0.007) መሻሻል አሳይተዋል፤ መካከለኛ የተጽዕኖ ደረጃም (eta squared = 0.077)
አሳይቷል፡፡ ከጥናቱ ግኝቶች በመነሳትም በአማርኛ ቋንቋ በሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮች መጻፍን
መማር የተማሪዎችን የመጻፍ ችሎታ ያዳብራል፤ ብሎም የመጻፍ ተነሳሽነት ያሻሽላል ወደሚል
ድምዳሜ ተደርሷል፡፡ ከግኝቶቹ በመነሳትም ስነትምህርታዊ የመፍትሄ ሀሳቦች ተጠቁመዋል፤
የወደፊት የምርምር አቅጣጫዎችም ተመላክተዋል፡