Abstract:
አህፅሮተ ጥናት (Abstract)
የዚህ ጥናት ዋና አላማ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት መማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ተማሪዎች ድርሰትን ለመጻፍ ያላቸው ግለብቃት እምነት እና ድርሰት በመጻፍ ችሎታቸው መካከል ያለውን ተዛምዶ መመርመር ነው፡፡ ጥናቱ ተዛምዷዊ ስልትን ተከትሏል፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን በጉባላፍቶ ወረዳ፣ በአሁንተገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በአንጎት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2010ዓ.ም በ9ኛ ክፍል ተመዝግበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል በእድል ሰጭ የንሞና ዘዴ የተመረጡ 205 ተማሪዎች ናቸው፡፡ የጥናቱን ዓላማ ከግብ ለማድረስም በጽሁፍ መጠይቅና በፈተና አስፈላጊ መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ ተማሪዎች በአማርኛ ቋንቋ ድርሰት ለመጻፍ ያላቸው ግለብቃት እምነት በመካከለኛ ደረጃ (61.85) ላይ እንደሚገኝ የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡ የተማሪዎች ድርሰት የመጻፍ ችሎታ ዝቅተኛ (29.27) ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች በአማርኛ ቋንቋ ድርሰት ለመጻፍ ያላቸው ግለብቃት እምነት ድርሰት ከመጻፍ ችሎታቸው ጋር አዎንታዊ ተዛምዶ(r=0.367,p<0.01**) አለው፡፡ በመሆኑም መምህራን በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ድርሰት የመጻፍ ትምህርትን በሚያስተምሩበት ጊዜ በተማሪዎች ድርሰት የመጻፍ ግለብቃት እምነት እና ድርሰት የመጻፍ ችሎታ መካከል አዎንታዊ ተዛምዶ መኖሩን በመረዳት የተማሪዎችን ድርሰት የመጻፍ ግለብቃት እምነት አስቀድመው ቢለዩና ከተማሪዎች ድርሰት የመጻፍ ችሎታ ጋር እንዲጣጣም ቢያደርጉ የተሻለ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችል የጥናቱ ውጤት ጠቁሟል፡፡