dc.description.abstract |
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በተማሪዎች አማርኛን የመማር ስልት እና የትምህርት ውጤት መካከል ያለውን ተዛምዶ፣ እንዲሁም የተማሪዎችን የመማር ምርጫ መመርመር ነው፡፡ ጥናቱ ተዛምዷዊ የምርምር ስልትን የተከተለ ነው። የጥናቱ ተሳታፊዎች በሙሎ ወረዳ ሆጀ ዱሬ ከተማ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል በኩራ ቀመሌ እና በጨራ ጉዲና አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ2014 ዓመተ ምህረት በዘጠነኛ ክፍል የሚማሩ 301 ተማሪዎች መካከል በቀላል እጣ ናሙና የተመረጡ 171 ተማሪዎች ነበሩ። የተማሪዎችን የመማር ስልት የሚመለከቱ መረጃዎች ከእነዚህ የጥናቱ ተሳታፊዎች በጽሁፍ መጠይቅ ተሰብስበዋል። የተማሪዎችን የመማር ውጤት የሚመለከቱ መረጃዎች ደግሞ ከመዛግብት ተወስደዋል። የጥናቱን ተዛምዶን የሚመለከቱ ሁለት ጥያቄዎች ለመመለስ ሲባልም የተሰበሰቡት መረጃዎችም በስፒርማን የተዛምዶ መወሰኛ ቀመር (Spearman correlation test) ተተንትነዋል፤ እንዲሁም የተማሪዎችን የመማር ስልት ምርጫ የሚመለከተውን የጥናቱን ሶስተኛ ጥያቄ ለመመለስ መረጃዎቹ በዳግም ልይይት ትንተና (እስከ ቤንፎረኒ ፖስት ሆክ ፍተሻ የሚዘልቅ) ተተንትነዋል። የጥናት የውጤት ትንተናው ውጤት (rs = 0.07፣ P=0.39) እንዳሳየው በተማሪዎች አጠቃላይ የመማር ስልት እና የትምህርት ውጤት መካከል ጉልህ ተማምዶ አልተገኘም፤ እንዲሁም አምስቱ የመማር ስልት ንኡሳን ክፍሎች (dimensions) አንድ ባንድ ከመማር ውጤት ጋር ያላቸው ስታትስቲክሳዊ ተዛምዶ በጣም ደካማ መሆኑን፣ እንዲሁም ጉልህነት እንደሌለው የተዛምዶ ውጤቶቹ (P>0.05) አመልክtተዋል። ከተማሪዎች የመማር ስልቶች ምርጫ አኳያ በስታትስቲክስ ጉልህ ልዩነት እንዳለ (ማለትም ተማሪዎች አንዱን ስልት ከአንዱ አስበልጠው እንደሚመርጡ) እስከ ቤንሮረኒ ፖስት ሆክ ቴስት ከዘለቀው የዳግም ልይይት ትንተና ውጤት (Wilks’ Lambda = 0.77, F(4,167) = 12.23, P < 0.001) መረዳት ተችሏል። ከዚህ ውጤትም ተማሪዎች ከአንዱ የመማር ስልት ይልቅ ለሌላው የመማር ስልት ያላቸው ምርጫ በስታትስቲክስ ጉልህ መሆኑ ታውቋል ማለት ነው። በዚህም መሰረት፣ የመማር ስልቶቹ የተማሪዎች ከፍተኛ ምርጫቸው ከሆኑት ዝቅተኛ ምርጫ ወደሆኑት ሲዘረዘሩ ቅደምተከተላቸው፤ አንደኛ፣ በመተንተን መማር፣ ሁለተኛ፤ በአውድ መማር፣ ሶስተኛ፤ በመተግበር መማር፣ አራተኛ፤ በማየት መማር እና አምስተኛ፤ በማዳመጥ መማር ሆኗል። በመሆኑም መምህራን በክፍል ውስጥ የአማርኛ ቋንቋን ሲያስተምሩ፣ ሌሎች የትምህርት ባለሙያዎችም በትምህርቱ የማስተማሪያ መሳሪያዎች ዝግጅት ላይ ሲሳተፉ ለመማር ስልቶች በዚሁ መሰረት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተጠቁሟል። |
en_US |