Abstract:
አህጽሮተ-ጥናት
የጥናቱ ዋና ዓላማ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ችግርፈች ዘዴ የተማሪዎችን የመፃፍ
ችሎታና የመፃፍ ተነሳሽነት ለማጎልበት ያለውን ሚና መፈተሽነው፡፡ ዓላማውን ለማሳካትም
ፍትነት መሰል (Quasi-experiment) የጥናት ንድፍ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ የጥናቱ
ተሳታፊዎች በምእራብ ጎጃም ዞን በጎንጅ ቆለላ ወረዳበጎንጅ የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶና
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ 2012 ዓ.ም በ11ኛ ክፍል ሲማሩ ከነበሩ በስምንት
መማሪያ ክፍል ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል በተራ እጣ ናሙና ዘዴ በተመረጡ ሁለት
መማሪያ ክፍልች የተገኙ 102 ተማሪዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም በችግርፈች ዘዴ መጻፍን
የሚማር ቡድንና በተለመደው መንገድ መጻፍን የሚማር ቡድን በማድረግ የመጻፍ ክሂል
ትምህርትን ለአስር ሳምንታት ተምረዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹም ቅድመትምህርትና
ድህረትምህርት የመጻፍ ችሎታ በፈተና፣ ቅድመትምህርትና ድህረትምህርት የመጻፍ
ተነሳሽነት መጠይቅ ተለክተው መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ በቅድመ ፈተና እና በቅድመ
የጽሑፍ መጠይቅ የተገኙ ውጤቶች በባለብዙ ልይይት ትንተና ዘዴ እንዲሁም በድኅረ
ፈተና እና በድኅረ የጽሑፍ መጠይቅ የተገኙ ውጤቶች በህብር ልይይት ትንተና ዘዴ
እንዲሰሉ ተደርጓል፡፡ የተገኙት ውጤቶች እንደሚያመለክቱት በቅድመ ፈተና እና በቅድመ
የጽሑፍ መጠይቅ ተመጣጣኝ አማካይ ውጤቶች የተመዘገበባቸው ቡድኖች፣ በድኅረ ፈተና
(ይዘት፣ አደረጃጀት፣ ቃላት፣ የቋንቋ አጠቃቀም እና ሥርዓተ አጻጻፍእና በድኅረ የጽሑፍ
መጠይቅ (ግለ ግንዛቤ፣ ግለ ብቃት እና ግለ መር) የሙከራ ቡድኑ ተማሪዎች ከቁጥጥር
ቡድኑ ተማሪዎች ጉልህ የሆነ ልዩነት አሳይተዋል (P= <0.05)፡፡ ይህም ውጤት ችግርፈች
ዘዴ የተማሪዎችን የመጻፍ ክሂል እና ተነሳሽነት ከማሻሻል አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ
እንዳለው ጠቁሟል፡፡ ከዚህም ውጤት በመነሳት መምህራን በችግርፈች ዘዴ እንዲያስተምሩ፤
የስርአተትምህርት ቀረጻ ባለሙያዎችም ዘዴውን እንደአንድ የማስተማሪያ ዘዴ አድርገው
እንዲያካትቱት ተጠቁሟል፡፡ በመጨረሻም ተመራማሪዎች ፊታቸውን ወደ ችግርፈች ዘዴ
እንዲያዞሩና ያልተዳሰሱ ክፍተቶችን እንዲሞሉ ለመጠቆም ተችሏል፡፡