Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በስነጽሁፍ ቴክስት ገጸባህርይተኮር የማስተማር ዘዴ የአንብቦ መረዳት ችሎታን ለማጎልበት ያለውን አስተዋጾ መመርመር ነው፡፡ ጥናቱ ከፊል ሙከራዊ ምርምር ስልትን ተከትሎ የተሰራና በአይነቱ ደግሞ መጠናዊ ምርምር ነው፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን በደጋዳሞት ወረዳ በፈረስቤት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ትምህርትቤት በ2011ዓመተ ምህረት ትምህርታቸውን በ39 ክፍሎች ተመድበው በመከታተል ላይ ከሚገኙ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በእድል ሰጭ ናሙና የተወሰኑት የዘጠነኛ ምድብ 2 ክፍል ተማሪዎች የሙከራ እና የዘጠነኛ ምድብ 28 ክፍል ተማሪዎች የቁጥጥር ቡድን በመሆን ነው፡፡ የተጠኝ ቡድን ተማሪዎችን የአንብቦ መረዳት ችሎታ ዳራ ለማወቅ በቅድሚያ ቅድመ ትምህርት ፈተና ተሰጥቷል፡፡ የተገኘው ውጤትም ተመጣጣኝ የአንብቦ መረዳት ችሎታ እንዳላቸው ያመለክታል፡፡ በመቀጠልም የጥናቱ ተሳታፊዎች የጥናቱን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በተዘጋጀው ቴክስት በተቃራኒ ፈረቃቸው በሳምንት ሁለት ቀን ለአራት ሳምንት ያህል እንዲማሩ ተደርጓል፡፡ ለጥናቱ የተዘጋጀው የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያ ፈተና ነው፡፡ በሂደቱም ቅድመትምህርት ፈተናና ድህረትምህርት ፈተና ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት በቅድመትምህርትና በድህረትምህርት የተገኙት የፈተና ውጤቶች በገላጭ ስታትስቲክስ በአማካይ፣ መደበኛ ልይይት፤ በነጻ ናሙና ቲ-ቴስትና በዳግም ልኬት ቲ-ቴስት ቀመር ተሰልቷል፡፡ በውጤት ትንተናው መሰረት የሙከራና የቁጥጥር ቡድኑ ድህረትምህርት ፈተና አማካይ ውጤት በነጻ ናሙና ቲ-ቴስት በስታትስቲክስ (p=.001) በመሆን ጉልህ ልዩነት (p < 0.05) ታይቷል፡፡ይህም በስነጽሁፍ ቴክስት፤ ገጸባህርይተኮር የማስተማር ዘዴ የአንብቦ መረዳት ችሎታን እንደሚያጎለብት አመላክቷል፡፡ እንዲሁም በሙከራ ቡድኑ ቅድመትምህርትና ድህረትምህርት ፈተና አማካይ ውጤት መካከል በዳግም ልኬት ቲ-ቴስት በስታትስቲክስ ጉልህ ልዩነት (p < 0.05) ታይቷል፡፡ በዚህም በስነጽሁፍ ቴክስት ገጸባህርይ ተኮር የማስተማር ዘዴ ለውጥ እንዳመጣ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ የጥናቱ ውጤትና ማብራሪያ እንደሚያሳየው በስነጽሁፍ ቴክስት ገጸባህርይተኮር የማስተማር ዘዴ የተማሪዎችን አንብቦ የመረዳት ችሎታ ለማጎልበት ጉልህ ሚና አለው፡፡ ይህም በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት፤በስነጽሁፍ ቴክስት ገጸባህርይተኮር የማስተማር ዘዴ የአንብቦ መረዳት ችሎታን ለማጎልበት አዎንታዊ ሚና አለውየሚልነው፡፡
ምዕራፍ አንድ፤ መግቢያ