Abstract:
አጠቃሎ
ይህ ጥናት ሚታዊ ንባብ በይስማዕከ ወርቁ ዴርቶጋዳ እና ራማቶሓራ ረጅም ልቦለዶች በሚል
ርዕስ የተደረገ ሲሆን የጥናቱ ዋና ዓላማ የተመረጡትን ልቦለዶች ከሚታዊ ሂስ አንፃር ማሳየት
ሲሆን ሁነታዊ ሚቶችን፣ ምልክታዊ ሚቶችን እና የሚት ተጋዳሊ ገጸባሕሪያትን ተንትኖ
ማሣየት ደግሞ ንዑሳን ዓላማው ነው፡፡ አጥኝዋ እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ሰነድ ፍተሻን
በመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴነት የተጠቀመች ሲሆን የመተንተኛ ስልቷ ደግሞ የጭብጥ ትንተና
ነው፡፡ እነዚህን የመረጃ መሰብሰቢያ እና መተንተኛ ዘዴዎች በመጠቀም በልቦለዶቹ ውስጥ
የሚታዩ ሁነታዊ ሚቶችን፣ ምልክታዊ ሚቶችን እና የሚት ተጋዳሊ ገጸባሕሪያትን ነቅሳ
በማውጣት ትንተና አድርጋለች፡፡ ሁነታዊ ሚትን ስትተነትን መታጨት፣ ፍለጋ እና ጉዞ
የሚሉትን የሚት ጭብጦች መነሻ ያደረገች ሲሆን በጉዞ ውስጥ ደግሞ መለየት፣ መነሳሳት እና
መመለስ የሚሉትን የጉዞ ደረጃዎች መሰረት በማድረግ ልቦለዶችን ተንትናለች፡፡ ምልክታዊ
ሚትን ስትተነትን ደግሞ ውሃ፣ ቀይ ቀለም እና ሰባት ቁጥርን በመውሰድ ውክልናቸውን
የተመለከተች ከመሆኑም ባሻገር ለልቦለዶቹ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አሳይታለች፡፡ እንዲሁም
ከሚታዊ ገጸባሕሪያት ውስጥ የተጋዳሊ ባህሪያትን የሚያሟሉ ዋና ተጋዳሊያንን በመለየት
በልቦለዶቹ ውስጥ የፈጸሙትን ተጋድሎ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ጥናቱ በልቦለዶቹ ውስጥ
የተነሱት ሚታዊ ጉዳዮች ታሪኩን ለማስተሳሰር የጎላ ሚና እንዳላቸው ከማመላከቱም ባሻገር
የታሪኩን ጭብጥ አጉልቶ ለማሳየት እና ለሃሰብ ማስኬጃነት እንዳገለገሉ አሳይቷል፡፡